Description
የሙስሊም ሕይወት መሠረታዊያን
መግቢያ
ማንኛውም ጠንካራ ሕንፃ በጥንካሬው ለመዝለቅ ጠንካራ መሠረት ሊኖረው ይገባል።
እስልምና መሠረቱ የቆመባቸው አምስት ምሰሶዎች ናቸው፤እነዚህም ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ በማለት እንዳስተማሩት፥ የኢስላማዊ አስተምህሮትን መሰረት ያዋቅራሉ፦
እስልምና በአምስት ምሰሶዎች ላይ የተገነባ ነው፦
1. የእምነት ቃለ ምስክር (ሸሃዳ)፣
2. መደበኛ ስግደት (ሰላት)፣
3. አመታዊ የልገሳ ክፍያ (ዘካ)፣
4. ረመዳን ወርን (በጨረቃ አቆጣጠር) መፆም (ፆም)፣
5. (ወደመካ) መንፈሳዊ ጉዞ (ሐጅ)።
እነዚህ አምስት ምሰሶዎች የሙስሊም ሕይወት የማዕዘን ድንጋይ ናቸው።
1. የእምነት ቃለ ምስክር - ሸሃዳ
የእምነት ቃለ ምስክር ማለት፥ ከአላህ በቀር ሊመለክ የሚገባው ሌላ አምላክ አለመኖሩንና ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የእርሱ አገልጋይና መልክተኛ መሆናቸውን መመስከር (ቃል መስጠት) ማለት ነው።
ይህም ከልብ በመነጨና ጥብቅ በሆነ እምነት ላይ መመስረት እንዲሁም በአንደበት በቃል መነገር ይኖርበታል።
የቃለ ምስክሩ የመጀመሪያ ክፍል ይህንን ያመለክታል፦
• አላህ ብቻ እንጂ ማንም ሰው፣ ቁስ ወይም ፍጡር የመመለክ መብት የለውም። "አላህ" የሚባለው አረብኛ ስም የሰው ዘር ሁሉ እና የየትኛውም ፍጥረተ አለም አንድዬና እውነተኛ አምላክ ይወክላል።
• አላህ ብቻውን የፍጥረተ አለሙ ሁሉ ፈጣሪ እና አኗሪ ሲሆን በሁሉም ነገር ላይ ስልጣን አለው።
• አላህ ብቻ የፍፁም ባህሪያት ባለቤት ሲሆን ከሁሉም አይነት እንከኖች የፀዳ ነው።
• አላህ አንድም አጋር፣ ብጤ፣ አባት፣ እናት አልያም ልጅ የለውም።
የቃለ ምስክሩ ሁለተኛ ክፍል ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የአላህ አገልጋይና የመጨረሻ መልክተኛ ስለመሆናቸው የሚገልፅ ነው።
እርሳቸው ሰዎችን አላህን ብቻ እንዲታዘዙና እንዲገዙ ጥሪ እንዲያደርጉ በተላኩ ረጅም የነቢያት ዝርዝር ውስጥ መደምደሚያው ነብይ ናቸው።
ከእነዚህ ነብያት መካከል ጥቂቶቹ አደም፣ ኑኅ፣ ኢብራሒም፣ ኢስማኤል፣ ይስሐቅ፣ ያዕቁብ፣ ዩሱፍ፣ ሙሳ፣ ዳውድ፣ ሱለይማን እና ኢሳ (ሰላም በሁላቸውም ላይ ይሁን) ናቸው።
ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ይሁን) የአላህን መልእክት ሰውን እንዲያስተምሩና ሁሉም ይከተለው ዘንድ በምሳሌ እንዲያገለግሉ ከቁርዓን (የመጨረሻው መለኮታዊ መፅሐፍ) ጋር ነበር የተላኩት።
የቃለ ምስክሩ አንዳንድ ጠቀሜታዎች፦
• ለአላህ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ እጅ መስጠትና የእርሱ እውነተኛ አገልጋይና ተገዥ መሆን፤
• ጨዋነት እና ትህትና ሳይጓደል፥ ከፍ ያለ የራስ አክብሮትን በራስ መተማመን ያመነጫል።
• ሰውን ጀግና፣ ደፋር እንዲሁም ተግባራዊ እና አቋም ያለው የሚያደርግ ጠንካራ ቁርጠኝነት፣ ትዕግስትና ትጋት ያመነጫል።
• ሰው የአላህን ትእዛዛት እንዲያከብርና እንዲጠብቅ ያደርጋል።
2. ስግደት - ሰላት
አምስቱ ዕለትዊ ሰላቶች በሙስሊም ሕይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የአምልኮ ሥርዓት ያዋቅራሉ፤ ንጋት ላይ፣ እኩለ ቀን ላይ፣ የተሲያት አጋማሽ ላይ፣ ፀሐይ እንደጠለቀች፣ እንዲሁም ማታ ላይ አንድ አንድ ጊዜ።
ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፦ “ሰላት የሐይማኖቱ (እስልምና) ምሰሶ ናት። ያቆማት ሐይማኖትን አቆመ፤ ያጠፋት (ምሳሌ፥ ችላ ያላት) ሐይማኖትን አጠፋ።”
ሰላት በሙስሊሙ እና በፈጣሪው መካከል እምነትን፣ ፍቅርን፣ ተስፋንና አክብሮትን መሰረት ያደረገ ግላዊና መንፋሳዊ ትስስርን ትዘረጋለች።
ሰላት በሙሉ ትኩረት፣ በመተናነስ እና በትህትና በትክክል ስትፈፀም፥ ልቡን በመብቃቃት፣ በሰላም እና በአላህ ቅርበት ሞልታ ሰውዬው ላይ ዘላቂ ውጤትን ታመጣለች።
"እኔ አላህ ነኝ። ያለ እኔ አምላክ የለምና ተገዛኝ። ሶላትንም (በእርሷ) እኔን ለማውሳት ስገድ።" ቁርዓን 20፡14
ሰላት የሙስሊም ሕይወት አስኳል ሲሆን ለአላህ ማደርን ለመጎናፀፍ ምርጡ መንገድ ነው።
ንፁህ በሆነ ማንኛውም ስፍራ - ሜዳ ላይ፣ በቢሮዎች፣ በፋብሪካዎች፣ አልያም በዩኒቨርሲቲዎች - ሊሰገድ የሚችል ሲሆን ጥቂት ደቂቃዎችን ብቻ ነው የሚፈጀው።
ከቅዱስ ቁርዓን ውስጥ የተወሰነ ንባብ፣ አላህን ማመስገንና ማወደስ፣ እንደ መቆም፣ ማጎንበስ፣ መስገድ እና መቀመጥ ከመሳሰሉ ልዩ ልዩ አካላዊ እንቅስቃሴዎች ጋር በውስጡ ያካትታል።
በሰላት አማካይነት፥ ሙስሊሙ የፈጣሪውን ታላቅነት ያስታውሳል እንዲሁም የፍላጎቱንና የምኞቱን እንዲሞላለት አቤት ይላል።
በአላህ ፊት በተደጋጋሚ ራስን ማዋደቅ ሰውዬውን ወደኃጢአት ከመግባት ያግደዋል፤ እናም ይህ ነፍስን የማጥሪያ አንድ መልክ ነው፥ ቁርዓን ውስጥ እንደተጠቀሰው “ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና።” (ቁርዓን 29፡45)
ሰላት የመፀፀት እና ይቅርታን ከአላህ የማግኛ እድልም ነው።
የአላህ መልዕክተኛ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሶሃቦቻቸውን እንዲህ በማለት ጠየቁ፦ “ከእናንተ አንዳችሁ በቀን አምስት ጊዜ የሚታጠብበት በበሩ የሚያልፍ ወንዝ ቢኖረው፥ ገላው ላይ ቅንጣት እድፍ ሊቀር ይችላልን?” “አይ።” ሲሉ መለሱ። ነቢዩም፡ እንዲህ በማለት አከሉ፥ "በተመሳሳይ አላህ በአምስቱ ዕለታዊ ሰላቶች ወንጀሎችን ያብሳል።”
3. የታዘዘ የእርዳታ መዋጮ - ዘካ
አደራ እንደሆነ የሚታሰበውን ሐብትን ጨምሮ፥ ሁሉም ነገር የአላህ ነው።
ትዕዛዛዊው የእርዳታ መዋጮ (ዘካ) የተወሰኑ መስፈርቶችን (ለምሳሌ፥ ለአቅመ አዳም መድረስ፣ አቅል ያለው መሆን፣ ከሆነ መጠን በላይ ሐብት ማካበት) በሚያሟላ ሙስሊም ላይ ሁሉ የተደነገገ ግዴታ ነው።
አንድ ሰው ከሚያፈራው አጠቃላይ አመታዊ ሐብት ውስጥ ጥቂት መጠን (ከጥሬ ገንዘብ ላይ 2.5% እና ምናልባትም ሌሎች ቋሚ ንብረቶችን ጨምሮ) ተሰልቶ ቁርዓን ባዘዘው መሰረት እርዳታው ለሚገባቸው አካላት (ለምሳሌ፥ ለድሆች እና ለችግርተኞች) ይወጣል።
ነቢዩ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፦ "ቀሪ ሐብታችሁን ሊያጠራላችሁ ፈልጎ ነው አላህ ዘካን ግዳጅ ያደረገው።"
"ዘካ" የሚለው ቃል ትርጉም ‘ማንፃት’ም እና ‘እድገት’ም ነው። ይህም ከተክሎች ጉንደላ ጋር ተመሳሳይ ነው። የተክሎች በመደበኛነት መከርከም የሚዛን መመጣጠን እንዲኖራቸውና እድገታቸው እንዲዳብር ያደርጋቸዋል።
ይህን ግዴታ በመሙላት ሙስሊሞች ቀሪ ሐብታቸውን ያጠራሉ እንዲሁም የፋይናንስም የመንፈስም እድገታቸውን ያረጋግጣሉ።
የዘካ አንዳንድ ጥቅሞች:
• ከራስ ወዳድነት፣ ከእብሪት እና ከስስት ልቦና ያነጻል።
• ለድሆችና ለችግርተኞች ማዘንን እና መራራትን ያለማምዳል።
• ሰውዬውን የአላህን በረከቶች ያስታውሰዋል ብሎም አመስጋኝ እንዲሆን ያበረታታዋል።
• በተለያዩ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ መደቦችና ቡድኖች መካከል ያለውን ልዩነት ያቀራርባል፤ እናም አንድ ራሱን የቻለ የማህበራዊ ዋስትና አይነት ነው።
• ሀብታሞች ከሐብታቸው ውስጥ የተወሰነውን እምብዛም ላልታደሉት እንዲያካፍሉ ግዴታ በማድረግ ድህነትን ይቀንሳል ብሎም እኩልነትን ያረጋግጣል፤ "... (ሀብት) ከእናንተ ውስጥ በሀብታሞቹ መካከል ተዘዋዋሪ እንዳይሆን።" ቁርዓን 59:7
በተጨማሪም አንድ ሰው ደስ ያለውን ያህል የውዴታ ሰደቃ ጨምሮ ሊለግስ ይችላል።
"ለእነዚያ ሶላትን አስተካክለው ለሚያደርሱት፣ ዘካንም ለሚሰጡት... እነዚያም እነርሱ ምኞታቸውን ያገኙ ናቸው።" ቁርዓን 31፡4-5
4. መፆም - ፆም
"እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና።" (ቁርዓን 2፡183)
እንደ ማንኛውም የአምልኮ ተግባር፥ ፆምም ከፍተኛ ቁርጠኝነትና ልባዊነትን በሚያሳይ ደረጃ ለአላህ ትዕዛዛት አክብሮት እና ሙሉ በሙሉ ማደርን ይፈልጋል። ዝንባሌ ከአላህ ትእዛዝ እና በታላቅ እርምጃ እና ከልብ ያለበለይ ተከታታይነት ይጠይቃል።
በየዓመቱ በረመዳን ወር (የጨረቃ አቆጣጠር 9ኛው ወር), ሙስሊሞች ከሶስት ቁልፍ ሰብዓዊ ፍላጎቶች - ከምግብ፣ ከመጠጥ እና ፆታዊ ግንኙነቶች - በመታቀብ ከማለዳ እስከ ጀምበር መግቢያ ይፆማሉ።
ሰውዬው ኃጢአት ከሆኑ ሁሉም ድርጊቶች ራሱን ማቀብም ይኖርበታል።
በረመዳን ወቅት መፆም አካላዊ እና አእምሯዊ ብቁነት ባለው እያንዳንዱ አዋቂ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው። ልጆች፣ ህመምተኞች፣ የአእምሮ ህሙማን፣ አረጋዊያን፣ የወር አበባ ላይ ያሉ ሴቶች፣ እና መንገደኞች ፆሙ አይመለከታቸውም።
የፆም አንዳንድ ጥቅሞች:-
• መንፈሳዊ ራስ-ማንፃትንና እድገትን ያበረታታል።
• በሳይንስ የተረጋገጡ የጤና ጠቀሜታዎች።
• በኑሮ እምብዛም ላልታደሉቱ ማዘን፣ ተጨማሪ ሰደቃን ማበረታታት።
• ራስን መቆጣጠርና ትዕግስትን የመማሪያ መንገድ።
• ነፍስን ያነጻል እናም ፍላጎቶችን በመገደብ ለአላህ የመገዛት ልማድን እንድትላበስ ይረዳታል ብሎም ቆራጥነትን ያበረታታል።
• በፆመኞች መካከል ከፍ ያለ የአንድነትና የጋራ ማንነት ስሜትን ይፈጥራል።
• አለም ስላለችበት ሁኔታ እና ስለተጋረጡት ተግዳሮቶች ከፍ ያለ ግንዛቤን ይፈጥራል።
• የኃጢአቶች ምህረት። ነቢዩ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፥ "አምኖና (የአላህን) ምንዳ ተስፋ አድርጎ ረመዳንን የፆመ ሰው፥ ያለፈ ወንጀሉ ይታበስለታል።"
5. (ወደመካ) መንፈሳዊ ጉዞ - ሃጅ
"ለአላህም በሰዎች ላይ ወደርሱ መሄድን በቻለ ሁሉ ላይ ቤቱን መጎብኘት ግዴታ አለባቸው።" (ቁርዓን 3፡97)
ወደተቀደሰችው መካ ከተማ (በሳውዲ ዓረቢያ የምትገኝ) እና ወደ ሌሎች ቅዱሳን ስፍራዎች በህይዎት ዘመን ቢያንስ አንድ ጊዜ መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግ ግድ ነው፤ የአካልም ሆነ የፋይናንስ አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ።
ሐጅ ማድረግ ማለት ሁሉንም አለማዊ ተግባራት በጊዜያዊነት ካቆሙ በኋላ በማስተንተን፣ በአምልኮ፣ የአላህን ምህረት በመፈለግ የእሱን ቅርበት የማሳኪያ ጊዜ ማለት ነው።
ሐጅ በጨረቃ አቆጣጠር 12ኛው ወር ላይ (በአረቢኛ ዙልሂጃ ወር) የሚካሔድ፥ ከሁሉም አይነት የቆዳ ቀለም፣ ዘር፣ ማህበራዊ ደረጃ እና የዕድሜ ክልል የመጡ ሰዎችን አንድዬውን እውነተኛ አምላክ በአብሮነት ሲያመልኩ በአንድነት የሚያስተሳስር አመታዊ ሁነት ነው።
ሁሉም ሰው በአላህ ፊት በእኩልነት ይቆም ዘንድ፥ ሐጃጆች ያላቸውን የማህበራዊም ሆነ የባህል ደረጃ ልዩነት የሚገፍ ቀላልና ተመሳሳይ ልብስ ይለብሳሉ።
ነቢዩ ሙሃመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አሉ፥ "ሐጅ ሲያደርግ ፀያፍ ንግግሮችን ያልተነፈሰ አልያም ሐጢዓት ያልሰራ፥ ልክ ከእናቱ ማህፀን እንደወጣ ሆኖ (ማለትም ከሐጢዓቶች ነፅቶ) ይመለሳል።”
የሐጅ ስነስርዓት፥ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዳስተማሩን በነቢዩ ኢብርሃም እግር መከተልን ያካትታል።
ይህ ታላቅ የአምልኮ ተግባር፥ እንሥሣ መሰዋትን፣ ዱዓ ማድረግን፣ የተለያዩ ስፍራዎች መጎብኘትንና በስፍራዎቹ መስገድን፣ ካዕባን መዞርን፣ በሁለት ተራሮች መሐል በእግር መጓዝን፣ እንዲሁም ሌሎች በርካት ስርዓተ አምልኮዎችን ጨምሮ በ6 ተከታታይ ቀናት ተከናውነው የሚፈፀሙ ብዙ ንዑሳን ግብሮችን በውስጡ ይይዛል።
ይህን መሰል ተሞክሮ ሕይወትን የሚቀይርና ሰዎችን ትሁት የሚያደርግ ሲሆን፥ ይበልጥ ታጋሾች እና አላህን አመስጋኝ ያደርጋቸዋል።
ልዩነታቸው የምንም ይሁን የምን፥ ሙስሊሞች ሁሉ አንድ ህዝብ እንደመሆናቸው መጠን፥ ወንድማማችነታቸው ይጨምራል።
መደምደሚያ
አምስቱ የአስልምና መሰረቶች በአላህ የተደነገጉ በመሆናቸው አንድ ሙስሊም ሊያምንባቸውና እንደታዘዙት ሊፈፅማቸው ይጠበቅበታል።
የሚተገበሩ እና ቀላሎች ናቸው፤ እናም ከኋላቸው ያለው ጥበብም ሆነ የሚያስገኙት በረከት መልከ ብዙ ነው።
ተገላብጠው ሲታዩ፥ የግለሰቡን ባህሪና ስነምግባር በማነፅ ብሎም ማህበረሰብንም ግለሰቦችንም ተጠያቂነት እንዲኖራቸውና ወደአላህ እንዲቃረቡ በማድረግ ለግለሰቡም ለማህበረሰቡም ደህና መሆን አስተዋፅዖ አላቸው።
እነዚህ የተከበሩ የእስልምና መሠረቶች ጠቀሜታቸው ሙሉ በሙሉ ለፍጡራኑ ነው፤ አላህ (ልቅና የተገባው ይሁን!) ከሁሉም ፍላጎቶች የጠራ ነው።
እነዚህ አምስት ምሰሶዎች ለሰው ዘር በመላ መሻሻልና ስኬት ጠንካራ መሰረት እና ‘የልምምድ ፕሮግራም’ ይሰጣሉ።
