Description
በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች
እስልምና ምንድነው? ሙስሊሞችስ እነማን ናቸው?
እስልምና አንድ ሰው ከአላህ እና ከፈጠራቸው ፍጡራን ጋር ያለውን ግንኙነት በሚገባ እንዲያጤን የሚያበረታታ ተፈጥሯዊና የተሟላ የህይወት መንገድ ነው። ማህበረሰቡንም ግለሰቡንም በሚጠቅሙ አላህ በፈቀዳቸው መልካም ተግባራት መፈፀም በኩል ነፍሶች እውነተኛ ደስታና ሰላም እንደሚያገኙ ያስተምራል።
የእስልምና መልእክት ቀላል ነው፤ በብቸኛው እውነተኛ አምላክ አላህ ማመንና እሱን ብቻ መገዛት፤ እንዲሁም ነቢዩ ሙሐመድን (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የመጨረሻ መልእክተኛው አድርጎ መቀበል። “ኢስላም” የሚለው ቃል ለአላህ ማደር ማለት ነው፤ተከታዮቹ ደግሞ ሙስሊሞች በመባል የሚታወቁ ሲሆን ከየትኛውም ዘር ወይም ብሔር የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ።
የሕይወት ዓላማ ምንድነው?
አላህ፥ ያለአላማ ዝም ብለን እንድንባዝን አይደለም የፈጠረን። ይልቁንስ ከፍ ያለ አላማ አለን – በፈጣሪያችን መመሪያ መሰረት እንኖር ዘንድ አላህን ማወቅና እሱን ብቻ መገዛት። ይህ መምሪያ በሁሉም ረገድ ስኬታማና የተቀደሰ ህይወትን፥ በዚህኛውም በቀጣዩም ዓለም፥ እንድንኖር ያስችለናል።
የአንድ ሰው እምነት የሚለካው የአሏህን ምልክቶች በማስተንተን ለይቶ ለማስተዋል አእምሮውን እና አመክንዮውን በመጠቀም ብቃቱ ብሎም በአላህ ትዕዛዝ መሰረት በመኖር ችሎታው ነው።
አላህ በላቀ ጥበቡ፥ የእሱን መንገድ እነማን በፈቃዳቸው እንደሚከተሉ ለመሞከር ለሰው ልጆች ነፃ ምርጫን ሰጥቷል።
አላህ ማን ነው?
አላህ የአንዱና እውነተኛው አምላክ መጠሪያ ስሙ ነው። አላህ ምንም አጋሮች፣ ብጤዎች፣ ወላጆች አልያም ልጆች የሉትም። ሁሉም የአላህ ባህሪያት (ስሞች) ምሉዕ ናቸው፤ ለምሳሌ፥ ፈጣሪው፣ እጅግ ሩህሩሁ፣ እጅግ ኃያሉ፣ እጅግ ፍትሐዊው፣ እጅግ ብልሁ እና ሁሉን አዋቂው። ከሰውም ሆነ ከቁስ ማንም የአላህን ጌትነትና መለኮታዊ ባህሪያት አይጋራም፤ ያም ሆኖ፥ እሱ ብቻ በቀጥታና በብቸኝነት መመለክ የተገባው ነው።
ሙሃመድ ማን ናቸው?
ሙሃመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አላህን በብቸኝነት እንዲገዛ ለሰው ዘር በመላ ጥሪ እንዲያደርጉ በተላኩ ረጅም የነቢያት ዝርዝር ውስጥ መደምደሚያው ነብይ ናቸው። አይነተኛ አባት፣ ባል፣ መምህር፣ መሪ እና ዳኛ፥ እንዲሁም እውነተኛ፣ ፍትሐዊ፣ አዛኝ እና ጀግና የሰው ዘር ምርጥ ምሳሌ ነበሩ። ምንም እንኳ በከፍተኛ ደረጃ የሚከበሩ ቢሆንም፥ እንደሌሎቹ ነቢያት ሁሉ፥ በሙስሊሞች አይመለኩም።
በአላህ ማመን ለምን?
በአላህ ለማመን፥ በቀላል ሎጂክ ላይ መመስረትን (ከታች ባጭሩ እንደቀረበው) እና መለኮታዊ ራዕይ መውረድን (በቀጣዩ ክፍል እንደተብራራው) ጨምሮ ብዙ ምክንያቶች አሉ።
የአፅናፈ አለሙ አጀማመር - በአላህ ለማመን ቀጥተኛ ሊባል የሚችል ምክንያት በአፅናፈ አለሙ ምንጭ ዙሪያ ፅብረቃ ከማድረግ ጋር ይያያዛል። አፅናፈ አለሙ በስተመጨረሻ ከየት ተገኘ? አፅናፈ አለሙ ሁሌም አልነበረም (መነሻ እንደነበረው ዘመናዊ ሳይንስ ያረጋግጣል) ብሎም ከምንም ነገር ሊገኝ አልያም ራሱን በራሱ ሊፈጥር አይችልም ነበር። ምክንያታዊ ድምዳሜ የሚሆነው ተፈጠረ ቢባል ነው። ከአፅናፈ አለሙ በተለየ፥ የአፅናፈ አለሙ ፈጣሪ፥ አላህ፥ ዘላለማዊ ነው፤ መጀመሪያ የለውም፤ እንዲሁም ሁልጊዜም ነበረ።
የአፅናፈ አለሙ ሥርዓት - በአላህ ለማመን ሌላ ቀላል ምክንያት የሚከተለውን ሎጂክ በመጠቀም ስለአፅናፈ አለሙ ስርዓት ማሰብ ነው፦
1. ስርዓት ያለው ማንኛውም ነገር ምጥቀትን ያሳያል
2. ሶላር ሲስተማችን ከተራቀቁ ኡደቶች፣ ህግጋትና ውቅሮች ጋር በከፍተኛ ደረጃ ስርዓዊ ነው
3. ስለዚህ፥ በአፅናፈ አለማችን ውስጥ ያለው ሥርዓት የፈጣሪን መኖር ብሎም ምጡቅነት ያሳያል
ቁርዓን ምንድን ነው?
ቁርዓን የአላህ ቀጥተኛ ቃል ሲሆን ለሰው ልጅ የወረደ የመጨረሻ መለኮታዊ ራዕይ ነው።
ቅዱስ ቁርዓን፥ ለእነዚያ ክፍት አዕምሮ ላላቸውና ቀናዒ ለሆኑት ፈጣሪ ለመኖሩ ጠንካራ ማሳመኛዎችን ያቀርባል።
በቋንቋ ስልቱ፣ በጥበቡ፣ በምክሮቹ፣ በውበቱ እና በርቱዕነቱ አቻ አይገኝለትም።
ቁርዓን፥ አላህ ለነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በመልዕክተኛው ጂብሪል በኩል ያወረደላቸው የራሱ ቀጥተኛ ቃል ነው፤ እናም እንደ ወንጌል እና ተውራት የመሳሰሉትን ሁሉንም ቀዳሚ ቅዱሳን መፃህፍት ይተካቸዋል።
የኢስላማዊ እውቀት ዋነኛው ምንጭ ነው።
በህይወት ስለመኖራችን አላማ፣ ስለትክክለኛው የአላህ ፅንሰ ሃሳብ፣ በአላህ ስለሚወደዱና ስለሚጠሉ ተግባራት፣ ስለነቢያት ታሪኮችና አስተምህሮቶቻቸው፣ ገነትን፣ ገሃነምንና የፍርዱን ቀን የተመለከቱ መግለጫዎችን የመሳሰሉ በርካታ ጉዳዮችን ያብራራል ብሎም ግልፅ ያደርጋል።
ከወረደበት ከ1400 በላይ ዓመታት ጀምሮ ተጠብቆ መቆየቱ እና አለመለወጡ ከቁርዓን ታላላቅ ተዓምራት ውስጥ አንዱ ነው።
በተጨማሪም፥ በዚያን ዘመን ሰዎች የማይታወቁ እና በቅርብ ጊዜ ብቻ የተደረሰባቸው ሳይንሳዊ እና ታሪካዊ እውነታዎችን በውስጡ ይዟል፤ ይህም ከአላህ ለመሆኑ አንድ ማረጋገጫ ነው።
የእስልምና ዋና ዋና ግብሮች ምን ምን ናቸው?
የመጀመሪያ ምሰሶ፥ የእምነት ምስክርነት።
ከአላህ ውጪ መመለክ የሚገባው ሌላ አምላክ አለመኖሩን እና ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የመጨረሻ መልእክተኛው መሆናቸውን ማወጅ
ሁለተኛ ምሰሶ፥ ሰላቶች
በቀን አምስት ጊዜ የሚፈፀሙ፡ ንጋት ላይ፣ እኩለ ቀን ላይ፣ የተሲያት አጋማሽ ላይ፣ ፀሐይ እንደጠለቀች፣ እንዲሁም ማታ ላይ አንድ አንድ ጊዜ
ሶስተኛ ምሰሶ፥ ዘካ
ይህ ለችግርተኞች በየአመቱ የሚፈፀም ግዴታዊ የችሮታ ክፍያ ሲሆን አንድ ሰው ከሚያፈራው አጠቃላይ አመታዊ ሐብት ውስጥ 2.5% ጥሬ ገንዘብ እና ምናልባትም ሌሎች ቋሚ ንብረቶችን ጨምሮ የሚሰላ ነው።
አራተኛ ምሰሶ፥ ረመዳን ወርን መጾም
ሙስሊሞች ከጀምበር መውጫ እስከ ጀምበር መግቢያ ሰአት ድረስ ማንኛውንም ምግቦችና መጠጦች ከመውሰድም ሆነ ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ተራክቦን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል።
አምስተኛ ምሰሶ፥ ሐጅ ማድረግ
አቅሙ የፈቀደ ማንኛውም ሙስሊም በህይወት ዘመኑ ቢያንስ አንዴ ወደ መካ በመጓዝ ሐጅ ማድረግ ይጠበቅበታል። ሰላት፣ ፀሎት፣ ምፅዋት፣ እና የእግር ጉዞን የሚያካትት ሲሆን በጣም አስተማሪና በመንፈሳዊነት የተሞላ ተሞክሮ ነው።
ሙስሊሞች ስለ ኢየሱስ እና ሌሎች ነቢያት ምን ያምናሉ?
አላህ በሺዎች የሚቆጠሩ ነቢያትን፥ ለእያንዳንዱ ህዝብ ቢያንስ አንድ አንድ፥ ከተመሳሳይ መልእክት ጋር ለዘመናት ልኳል፤ አላህን በብቸኝነት መገዛትና ከእሱ ጋር ምንንም ነገር አለማጋራት።
ከእነዚህ ነቢያት መካከል የተወሰኑት፦ አደም፣ ኑህ፣ ዩሱፍ፣ ኢብራሒም፣ ያዕቁብ፣ ይስሐቅ፣ ሙሳ፣ ኢሳ እና ሙሐመድ (ሰላም በሁሉም ላይ ይሁን) ይገኙበታል።
ኢየሱስ ያለ አባት በተዓምራዊ መንገድ የተወለዱ ሲሆን በርካታ ተዓምራትን ፈፅመዋል – ሁሉም በአላህ ፈቃድ።
ኢየሱስ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በሐያሉ አላህ ከተላኩት እጅግ ታላላቅ ነቢያት መካከል አንዱ ነበሩ።
ኢየሱስ አምላክ አልያም የአምላክ ልጅ ወይም የስላሴ አካል አይደሉም፥ ይህ እስልምና ስለአምላክ ካለው ንፁህ አስተምህሮት ጋር በግልጽ ስለሚጋጭ።
የሚከተለውን ልብ ይበሉ:
• አምላክ ከእርሱ የተለየ አካል እንደሆነ አድርጎ ኢየሱስ የሚናገርባቸው እና ባህሪውን የሚገልፅባቸው በርካታ ምሳሌዎች በክርስትና አስተምህሮቶች ውስጥ አሉ፤ ለምሳሌ የኢየሱስ ለአምላክ መፀለይ - ኢየሱስ አምላክ ከነበረ፥ ለማን ሊሆን ይችላል ሲፀልይ የነበረው?
• "የአምላክ ልጅ" የሚለው አገላለፅ በጥንታዊያኑ የመፅሃፍ ቅዱስ ቋንቋዎች - ለኢየሱስ ለብቻው ሳይሆን - ለብዙ “አምላክን ፈሪ” ሐይማኖተኛ ሰዎች በተምሳሌታዊ መገለጫነት ጥቅም ላይ ውሏል። ችግሩ የሚከሰተው አገላለፁ ቃል በቃል አልያም በሌሎች መንገዶች ጥቅም ላይ ሲውል ነው።
ምንም እንኳ ሙስሊሞች ኢየሱስን (እና ሌሎቹን ነቢያት በሙሉ) የሚወዷቸውና የሚያከብሯቸው ቢሆንም፥ እሳቸውን አያመልኩምም መለኮታዊ ባህሪያትን አይሰጧቸውም - ምክንያቱም ይህ ለአላህ ለብቻው የተተወ ነውና።
ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ አይነት ናቸውን?
መልካም ስነምግባርን እና ለሌሎች ደግ መሆነን ወዘተ. በተመለከተ አብዝኞቹ ሐይማኖቶች በጥቅሉ ተመሳሳይ አስተምህሮቶች ቢኖሯቸውም፥ እስልምና በተጨማሪም በአንድነቱና በምሉዕነቱ ዙሪያ ያለምንም ማቃለል የአላህ ታላቅነት ላይ ያተኩራል።
ከሌሎች ሃይማኖቶች በተለየ፥ እሱ ከፈጠረው ፍጥረተ ዓለም ጋር ሲነፃፀር አላህ ሙሉ በሙሉ የተለየና ብቸኛ እንደሆነ እንዲሁም ምስጋና እና አምልኮ ሁሉ ለእሱ በቀጥታና ለብቻው ሊደረግ የተገባ እንደሆነ እስልምና በቀዳሚነት ያስተምራል።
በተጨማሪም እስልምና ባህር ነው፤ ቀላል ግን ጥልቅ ነው፤ ተጠብቆ የኖረ መለኮታዊ መፅሃፍ አለው፤ የአላህን ነቢያት አንዱንም አይንቅም፥ ሁሉም ግን ከአንድና ተመሳሳይ መልዕክት ጋር መላካቸውን ያስቀምጣል።
ከሞት በኋላ ምን አለ?
ሞት አጭር ከሆነው ይህ ሕይወት ዘላለማዊ ወደሆነው ቀጣይ ሕይወት የሚደረግ ሽግግር ነው። በፍርዱ ቀን እያንዳንዱ ሰው ከቀብር ተቀስቅሶ በስራው ተጠያቂ ይሆናል።
አንድ ሰው አላህን በማምለክና በመታዘዝ መልካምና የተከበረ ህይወትን ከኖረ፥ በአላህ እዝነት ወደገነት የሚገባ ይሆናል።
አላህን መካድ የመረጠ፥ የገሃነም እሳት ይጠብቀዋል።
በጎ ሰሪዎች የሚመነዱበትና ክፉ ሰሪዎች የሚቀጡበት ቀጣይ ዓለም ባይኖር ኖሮ፥ ከአላህ ፍጹም ፍትሐዊነት ጋር የሚጣረስ ይሆን፥ ህይወትም ኢሚዛናዊ ትሆን ነበር።
እስልምና ሴቶችን እንዴት ይመለከታል?
በእስልምና ውስጥ፥ ወንዶችና ሴቶች በአላህ ፊት በእኩል አይን ይታያሉ፥ እኩል ምንዳዎችን ከመመንዳትም ሆነ ለሚፈፅሟቸው ወንጀሎች ከሚኖራቸው ተጠያቂነት አንፃር።
ሁለቱንም ጾታዎች የፈጠረው አላህ፥ ልዩነቶቻቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው የተለያዩ ሚናዎችን እና ሐላፊነቶችን ሰይሞላቸዋል።
ሴቶች፥ ምንም አይነት ጭቆና በእነሱ ላይ ሳይጫንባቸው፥ ከፍተኛው ሞገስ እና ክብር ተሰጥቷቸዋል።
የውርስ ኃጢአት ፅንሰ ሀሳብ በእስልምና ውስጥ አለ?
የውርስ ኃጢአት ፅንሰ ሀሳብ በእስልምና ውስጥ የለም። አላህ ፍትሃዊ ነው፤ በመሆኑም አንድም ሰው ራሱ ኃላፊነት በማይወስድበት ማንኛውም ኃጢአት ተጠያቂ አይሆንም።
ጂሃድ ምንድነው?
የጂሃድ ፍሬ ነገር አምላክን በሚያስደስት መልኩ ለሐይማኖት ተጋድሎ ማድረግ እና መስዋዕትነት መክፈል ነው።
ከስነልሳን አንፃር "ተጋድሎ" ማድረግ ማለት ሲሆን መልካም ስራዎችን ለመስራት፣ በጎ አድራጎትን ለመፈፀም አልያም ኢስላማዊ ውትድርናን ለመቀላቀል መታተርን ሊያመለክት ይችላል።
በጣም በስፋት የሚታወቀው፥ የማህበረሰብን ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የጭቆና መንሰራፋትን ለመግታት እና ፍትህን ለማረጋገጥ የሚፈቀደው ወታደራዊው የጂሃድ አይነት ነው።
እስልምና ሽብርተኝነትን ይፍቀድ ይሆን?
በጦርነት ወቅት፥ ፍልሚያ ላይ የማይሳተፉ ንፁሃን ዜጎችን ኢላማ ማድረግ እስልምና በግልፅ የሚከለክለው ውግዝ ተግባር ነው።
እንዲያውም፥ ሙስሊሞች ንፁሃን የሰው ልጆችን ይቅርና ዕፅዋትንና እንስሳትን እንኳ ያለምክንያት እንዲያወድሙ አልተፈቀደላቸውም።
ይህ ግን በእስልምና ከተደነገጉ በርካታ የጦርነት ስነምግባራዊ መመሪያዎች መካከል አንድ ምሳሌ ነው።
ሆኖም ግን፥ ሽብርተኝነትን ህጋዊ ከሆነ ወረራን የመቃወም ተጋድሎ ለይቶ መመልከት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ሁለቱ በጣም የሚለያዩ ጉዳዮች ስለሆኑ።
ሃላል ምግብ ምንድን ነው?
ሃላል፥ ወይም ህጋዊ፥ ምግቦች እነዚያ አላህ ለሙስሊሞች እንዲጠቀሟቸው የተፈቀዱ ናቸው።
በአጠቃላይ፥ አብዛኞቹ ምግቦችና መጠጦች ሃላል ተደርገው ይወሰዳሉ፤ በዋናነት የተከለከሉት አሳማና አልኮል ናቸው።
የሥጋ ከብቶችና ዶሮ ሰብዓዊነትን በተላበስና በትክክለኛ መንገድ መታረድ ይኖርባቸዋል፤ ይህም ከእርድ በፊት የአላህን ስም መጥራት እና የእንስሶቹን ስቃይ መቀነስን ይጨምራል።
ማን ሙስሊም ሊሆን ይችላል?
አላህ የእስልምናን በሮች ለመላው የሰው ልጆች፥ የቀድሞውም ሆነ የአሁን ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን፥ ክፍት አድርጓል።
ስለዚህ፥ ማንኛውም ሰው በየትኛውም ጊዜ በቀላሉ በማመንና የሚከተለውን የእምነት ምስክርነት ቃል በመናገር ሙስሊም መሆን ይችላል፥
‘ከአላህ በስተቀር ሊመለክ የሚገባው ሌላ አምላክ አለመኖሩን እመሰክራለሁ፤ እንዲሁም ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ።’
ሙስሊም መሆን ማለት የፈጣሪን ልቅና ማወቅና ለእርሱ በመታዘዝ ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ማዳበርና ማስጠበቅ ማለት ነው።
ይህም በዚህኛው ሕይወትና በቀጣዩ ደስታንና እርካታን ያመጣል፤ እናም የሰውዬው የህይወት አላማ እውን ይሆናል።
