ሞት እና የወዲያኛው ዓለም በእስልምና

11.83 MB 58 1 Files
albyan
or download free
[free_download_btn]

Description

"ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት።" ቁርዓን 29:57

ሞት ቅርብ ነው

"የትም ስፍራ ብትሆኑ በጠነከሩ ሕንጻዎች ውስጥ ብትሆኑም እንኳ ሞት ያገኛችኋል። . . ." ቁርዓን 4:78

ሞት ማንም ሊያመልጠው የማይችል እውነታ ነው። በየቀኑ፣ በየሰዓቱ፣ በየደቂቃው ይበልጥ እየቀረበ ይመጣል። በሲ.አይ.ኤው የ2007ቱ ዘ ወርልድ ፋክት ቡክ ዘገባ መሠረት፥ በየሰከንዱ ሁለት የሚሆኑ ሰዎች ይሞታሉ። ይህም በየአመት የሚያስደነግጥ 57.9 ሚሊዮን ሰዎች ማለት ነው! እያንዳንዱ ፍጡር ዕድሜው፣ ጤናው፣ የኋላ ታሪኩ፣ ማህበራዊ ደረጃው አልያም መንፈሳዊነቱ ምንም ይሁን ምን ከዚህ የማይቀር ፍርጃ ላይ ይደርሳል። የቀድሞዎቹ ነገስታት፣ ባለጠጎች እና ኃያላን የት ነው ያሉት? በአንድ ወቅት አማላይ፣ ስመ ጥር እና ሊቃውንት የነበሩትስ የት ነው ገቡ?

የሞት እውንነት

ሞት መቅሰፍት አይደለም፤ ከዚህኛው ዓለም ወደ ቀጣዩ ዓለም የሚደረግ ሽግግር እንጂ።

ስለሕይወት ፋይዳ እና ከሞት በኋላ ስለምንሆነው ነገር ቆም ብለን እንድናስብና እንድናሰላስል ሊያደርገን ይገባል።

አላህ (አምላክ) የፈጠረን እርሱን ብቻ ለመገዛት አላማ እንደሆነና ምድራዊውን ህይዎት ማን ይህን አላማ እንደሚያሟላ መፈተኛ እንዳደረገው ቅዱስ ቁርዓን ውስጥ ገልፆልናል፤

"ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።" ቁርዓን 51:56

ሞትና ሕይወት የተፈጠሩት ለምን እንደሆነም አላህ አሳውቆናል።

"ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መሆኑን ሊሞክራችሁ ሞትንና ሕይወትን የፈጠረ ነው።" ቁርዓን 67:2

አንድ ሰው ለስርዓተ ቀብር ማስፈፀሚያ አገልግሎት አልያም ለአስክሬን ሳጥን ቅድሚያ ክፍያ በመፈፀም ለሞት አይሰናዳም።

ቁም ነገሩ የተፈጠሩበትን የሕይወት አላማ ስለማሟላት ነው - አላህን ብቻ ስለመገዛት፣ በእርሱ ትዕዛዛት መሰረት ስለመኖር፣ እንዲሁም በጎ ተግባራትን ስለመፈፀም።

በእስልምና ውስጥ የአምልኮ ፅንሰ ሃሳብ ሁሉን አቀፍ ሲሆን እንዲሁ በደፈናው በመስገድ ብቻ የተወሰነ አይደለም።

እንዲያውም፥ አላህ የሚወደው ማንኛውም ስራ እንደ አምልኮ ተግባር ነው የሚታየው፤ ብሎም በጎ ሰሪ በስራው ምንዳን ያገኝበታል።

የሞት ቅፅበት

"ማንኛይቱም ነፍስ ለነገ ያስቀደመችውን ትመልከት።" ቁርዓን 59:18

የሞት ምሳሌዎችን በያንዳንዷ ዕለት እናያለን።

ስቃይም ሆነ ነውጥ የሌለበት ሞት ሰላማዊ ይመስለናል።

ነገር ግን፥ ጉዳዩ የግድ እንደዚያ ላይሆን ይችላል።

ሰው ሲሞት ነፍሱ ከሥጋው ትነጠላለች፤ ስለዚህ የስጋው አካላዊ ገፅታ ነፍሱ የምትገኝበትን ሁኔታ ላያንፀባርቅ ይችላል።

የነፍስ ሰላማዊነት አልያም መረባበሽ ሰዎች የምድራዊ ህይዎት አላማቸውን በተገቢው የመወጣት አለመወጣታቸው ቀጥተኛ ውጤት ነው የሚሆነው፤ እናም ከሞት መንስዔ ጋር ያለው ግንኙነት ኢምንት ነው።

ከዚህ በፊት ሄደው ወደማያውቁበት መዳረሻ የሚወስዳቸውን የጉዞ ቲኬት የያዙ ሁለት ሰዎችን ምሳሌ ይመልከቱ።

የመጀመሪያው ሰው ስለሚሄድበት አገር ቋንቋ፣ ባህል እና ልማዶች ለመማር ጊዜውን ይሰዋል።

ትክክለኛውን የገንዘብ ምንዛሬ ያዘጋጃል፤ አስፈላጊ ክትባቶችን ይወስዳል፤ የጉዞው ሰዓት ሲደርስም ጥንቅቅ ብሎ ይገኛል።

ይህ ሰው በስነስርዓት ጊዜውን ወስዶ ዝግጅቱን ስላደረገ ደህነኛም ደስተኛም ነው።

በተቃራኒው፥ ሁለተኛው ሰው ዝግጅት ላይ ግዴለሽ ሲሆን ለጉዞ የሚነሱበት ሰዓት እስኪደርስ ድረስ እንዲሁ ያለሃሳብ ይኖራል።

ወዳልታወቀው መዳረሻ ስፍራ በፍርሃት እና ግራ መጋባት ውስጥ ሆኖ ይደርሳል።

ዝግጅት አለማድረጉ ለሚያስጠላ እጣ ፋንታ ይዳርገዋል፤ ይዟቸው የመጣው ነገሮች በሙሉ ፋይዳ ቢስ ይሆናሉና።

ይህን የመሰለውን በዋል ፈሰስ የሆነ ሰው ሲገልጽ አላህ በቁርዓን እንዲህ ይላል።

"አንዳቸውንም ሞት በመጣበት ጊዜ እንዲህ ይላል ‘ጌታዬ ሆይ! (ወደ ምድረ ዓለም) መልሱኝ። በተውኩት ነገር በጎን ሥራ ልሠራ እከጅላለሁና።’ (ይህን ከማለት) ይከልከል። እርስዋ እርሱ ተናጋሪዋ የኾነች ከንቱ ቃል ናት።"

ቁርዓን 23:99 -100

በተጨማሪም የእነዚያን ወደ ጀሃነም የተላኩት ሰዎች ለዚያ የዳረጋቸው ምን እንደሆነ በተጠየቁ ጊዜ ምላሻቸውን ያጢኑ፤

"(እነርሱም) ይላሉ ‘ከሰጋጆቹ አልነበርንም። ለድሆችም የምናበላ አልነበርንም።

ከዘባራቂዎቹም ጋር እንዘባርቅ ነበርን። በፍርዱ ቀንም እናስተባብል ነበርን።

እርግጠኛው (ሞት) እስከ መጣን ድረስ።’" ቁርዓን 74፡43-47

ሁላችንም የተቆረጠች ዕለተ ሞት አለችን፤ እናም ሁላችንም ወደዚያ እንግዳ መዳረሻ እንጓዛለን። ራስዎን ይጠይቁ፥ ለዚያ ተዘጋጅተዋልን?

የሕይወት ዓላማ

“የፈጠርናችሁ ለከንቱ መሆኑን እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መሆናችሁን ጠረጠራችሁን? (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?)” ቁርዓን 23፡115

ሕይወት በሞት የሚጠናቀቅ ፈተና ነው፤ ነገር ግን ሞት የአንድን ሰው ህልውና ማክተም አያመለክትም።

ሞት እንደመጣ፥ በጎ ምግባር የመፈፀሚያ እድል ይቋረጣል።

ለመፀፀት ጊዜው ይረፍዳል፤ እናም እጣ ፋንታችን በእምነታችን እና አሁን በምንኖረው ህይወት በምንፈፅማቸው ተግባራት ብቻ ይወሰናል።

የሰው ልጅ ሕይወት በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ነው፤ የዚህኛው አለም አጭር ቆይታ እና የቀጣዩ ዘላለማዊ ሕይወት።

ማንኛውም ጤነኛ አእምሮ ዘላለማዊ ሐሴት ምድር ላይ በአጭሩ ከሚቋጩ መደሰቶች እጅግ ሲበዛ ጠቃሚ መሆኑን ይደመድማል።

አላህ የሰው ዘርን ፈጥሮ ነፃ ምርጫን እና ትክክልን ከስህተት የሚለይበት አእምሯዊ ብቃት በመስጠት ለሥራዎቻችን ተጠያቂ እንድንሆን አድርጎናል።

በጎ ሰሪዎች የሚመነዱበትና ክፉ ሰሪዎች የሚቀጡበት ቀጣይ ዓለም ባይኖር ኖሮ፥ ከአላህ ፍጹም ፍትሐዊነት ጋር የሚጣረስ ይሆን ነበር።

ስለዚህ እያንዳንዷ ነፍስ በስራዋ የምትጠየቅበት የፍርድ ቀን መኖር የፍፁማዊ ፍትህ ጥያቄ ጉዳይ ነው።

"ሙስሊሞቹን እንደ ከሓዲዎች እናደርጋለን? ለእናንተ ምን (አስረጅ) አላችሁ? እንዴት ትፈርዳላችሁ?” ቁርዓን 68፡35-36

የፍርዱ ቀን

«’ያ ከእርሱ የምትሸሹት ሞት እርሱ በእርግጥ አግኛችሁ ነው። ከዚያም ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ ወደሆነው ጌታ ትመለሳላችሁ። ትሠሩትም የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል’ በላቸው።» ቁርዓን 62፡8

የሁሉም ሰው የዚህ ዓለም ህይወት ስራዎች በዝርዝር ተመዝግበው ይቀመጣሉ፤ አላህ እንዲህ ይላል፡

"(ለሰው ሁሉ) መጽሐፉም ይቀርባል። ወዲያውም ከሓዲዎችን በውስጡ ካለው ነገር ፈሪዎች ሆነው ታያቸዋለህ። «ዋ ጥፋታችን! ለዚህ መጽሐፍ (ከሥራ) ትንሽንም ትልቅንም የቆጠራት ቢሆን እንጂ የማይተወው ምን አለው» ይላሉም። የሰሩትንም ነገር ሁሉ ቀራቢ ሆኖ ያገኙታል። ጌታህም አንድንም አይበድልም።” ቁርዓን 18፡49

በእንዲህ ያለው ሁሉንም ስራዎቻችንን ዘርዝሮ በያዘ መዝገብ ትክክለኛነት እንደነቃለን፤ ገና ድሮ የረሳናቸውን ጉዳዮች ሁሉ ስለሚያስታውሰን። አላህ እንዲህ ይላል

"የሠሩትንም ሁሉ ይነግራቸዋል። የረሱት ሲሆኑ አላህ ዐውቆታል።" ቅዱስ ቁርዓን 58፡6

በዚህ ላይ በጥልቀት ስናውጠነጥን፥ እንደሚመዘገብብን እና ነገ በፍርዱ ቀን ከአላህ ፊት እንደሚጋለጥብን እያወቅን ማንኛውንም ሐጢያት መስራት በራሳችን እንድናፍር ሊያደርገን ይገባል።

ለእነዚያ የአላህን ከቀብር የማስነሳትና ለፍርድ የማቅረብ ችሎታዎች ለሚጠራጠሩ፥ ኢአማኞችን የሚሉትን አላህ ይጠቅሳል፤

"’አጥንቶችን እነርሱ የበሰበሱ ሲሆኑ ሕያው የሚያደርጋቸው ማነው? ያ በመጀመሪያ ጊዜ (ከኢምንት) ያስገኛት ሕያው ያደርጋታል። እርሱም በፍጡሩ ሁሉ (ሁኔታ) ዐዋቂ ነው’ በላቸው።" ቁርዓን 36፡78-79

ጀነት እና ጀሐነም

እነዚያ አላህ ሊመለክ የሚገባው ብቸኛ አምላክ መሆኑን አምነው በጎ ተግባራትን የሚፈፅሙ፥ እነርሱ ጀነትን ይሸለማሉ።

“የገነት ሰዎች ዛሬ በእርግጥ በሥራዎች ውስጥ ተደሳቾች ናቸው። እነርሱም ሚስቶቻቸውም በጥላዎች ውስጥ ናቸው። ባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ተደጋፊዎች ናቸው። በውስጧ ለእነርሱ ፍራፍሬዎች አሏቸው። ለእነርሱም የሚፈልጉት ሁሉ አልላቸው።” ቁራዓን 36፡55-57

ነቢዩ ሙሀመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አላህ እንዲህ ማለቱን አስተላልፈዋል፥

“ዐይን አይቷቸው፣ ጆሮ ሰምቷቸው፣ የሰው ልጅ ልብ አስቧቸው የማያውቃቸው እጅግ ምርጥ ነገሮችን ለደጋግ ባሮቼ አዘጋጅቻለሁ።”

ይህ የአላህን አንድነት የካዱ ሰዎች ከሚጠብቃቸው ነገር ጋር በቀጥታ የሚቃረን ነው፤ እነርሱም እንዲህ ይባላሉ፡

“ይህቺ ያቺ ትቀጠሩዋት የነበረችው ገሀነም ናት። ትክዱ በነበራችሁት ምክንያት ዛሬ ግቧት (ይባላሉ)።” ቁርዓን 36:63-64

ለካሐዲዎች ከቅጣቶች ሁሉ እጅግ የከፋው ይጠብቃቸዋል።

ገሀነም መጠባበቂያ (ስፍራ) ናት። ለሕግ ተላላፊዎች መመለሻ ስትሆን። በውስጧ ብዙን ዘመናት ነዋሪዎች ሲሆኑ፤ በውስጧ ቅዝቃዜንም መጠጥንም አይቀምሱም። ግን ሙቅ ውሃንና እዥን (ይቀምሳሉ)። ተስማሚን ምንዳ ይምመነዳሉ።እነርሱ ምርመራን የማይፈሩ ነበሩና። በአንቀጾቻችንም ማስተባበልን አስተባበሉና። ነገሩንም ሁሉ የተጻፈ ሲሆን አጠቃለልነው። ቅመሱም ቅጣትንም እንጂ (ሌላን) አንጨምራችሁም (ይባላሉ)።” ቁርዓን 78፡21-30

ማጠቃለያ

"አንተ ሰው ሆይ! በቸሩ ጌታህ ምን አታለለህ? በዚያ በፈጠረህ አካለ ሙሉም ባደረገህ ባስተካከለህም። በማንኛውም በሻው ቅርፅ በገጣጠመህ (ጌታህ ምን አታለለህ)። ተከልከሉ፤ በእውነቱ በፍርዱ ቀን ታስተባብላላችሁ።” ቁርዓን 82፡6-9

"እውነተኞቹ ምእምናን በእርግጥ በገነት ውስጥ ናቸው።ከሓዲዎቹም በእርግጥ በገሀነም ውስጥ ናቸው።" ቁርዓን 82፡13-14

ሞት አይቀሬ ነው። የሕይወት ዓላማችን አላህን ብቻ መገዛት፣ ደጋግ ተግባራትን መፈፀም እና ከተከለከሉ ነገሮች መከልከል ነው። አሁን ላይ በምንፈፅማቸው ተግባራት መሰረት እጣ ፋንታችን እየተወሰነ ነው። ስለዚህ ምድር ላይ የተሰጡንን እድሎች ገነት ውስጥ ዘላለማዊ ስፍራን ለማረጋገጥ ልናውላቸው አልያም ዝም ብለን አባክነናቸው ዘላለማዊ የገሃነም ቅጣትን በራሳችን ላይ ልንፈርድ ይቻለናል።

Similar Downloads

No related download found!