የሰይጣን ወጥመዶች مكائد الشيطان

6.07 MB 47 1 Files
albyan
or download free
[free_download_btn]

Description

"ሰይጣን ለናንተ ጠላት ነው። ስለዚህ ጠላት አድርጋችሁ ያዙት።..." ቁርዓን 35:6

ብልህ ሰው ብሎ ማለት የጠላቶቹን ስልቶች አጥንቶ እነርሱን ለማሸንፍ ቅድመ ጥንቃቄዎችንና እርምጃዎችን የሚወስድ ነው።

ጌታችሁ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋችኋል፥ "ሰይጣን ለናንተ ጠላት ነው። ስለዚህ ጠላት አድርጋችሁ ያዙት።..." ቁርዓን 35:6

የሰይጣን (ኢብሊስ) ታሪክ

ሰይጣን የተፈጠረው ከጪስ አልባ ነበልባል እሳት ነበር። እርሱ መልዓክ ባይሆንም፥ ለአላህ (አምላክ) ታዛዥ በመሆኑ ምክንያት በሰማይ ቤት አብሯቸው ይኖር ነበር።

አላህ ነቢዩ አደምን (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሲፈጥር፥ በሰማይ ቤት ያሉትን ሁሉ ለአደም እንዲሰግዱ አዘዘ፤ ነገር ግን ሰይጣን በኩራትና በእብሪት ተወጥሮ እንዲህ በማለት አሻፈረኝ አለ፥ "’እኔ ከርሱ የበለጥኩ ነኝ፡፡ ከእሳት ፈጠርከኝ፡፡ እርሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው’ አለ፡፡" (ቁርዓን 7:12)

አላህ ሰይጣንን ረገመውና ከሰማይ ቤት አበረረው። ሰይጣን የሰው ዘርን ለማሳሳት እድል እንዲሰጠው ለመነ፥ አላህም ልመናውን ፈቀደለት።

“’ስለአጠመምከኝም ለእነርሱ በቀጥተኛው መንገድ ላይ በእርግጥ እቀመጥባቸዋለሁ’ አለ፡፡ ‘ከዚያም ከስተፊቶቻቸው ከኋላቸውም ከቀኞቻቸውም ከግራዎቻቸውም በእርግጥ እመጣባቸዋለሁ፡፡ አብዛኞቻቸውንም አመስጋኞች ኾነው አታገኛቸውም’ (አለ)፡፡ (ቁርዓን 7:16-17)

የሰይጣን ወጥመዶች

በአላህ አንድነት መካድ

የእስልምና ስረ መሰረት በአላህ አንድነት ማመን ነው፤ አላህ አጋርም፣ ብጤም፣ ልጅም ሆነ ተቀናቃኝ የለውም። በግልባጩም፥ እጅግ ከፍተኛው ሐጢዓት በአላህ ላይ አጋሮችን ወይም ብጤዎችን ማበጀት ነው።

ምሳሌዎች ቀጣዮቹን ያካትታሉ፦

· አምልኮን ከአላህ ውጪ ላለ ነገር ማድረግ (ለምሳ፥ከአላህ ሌላ ለሆነ ነገር መስገድ ወይም መፀለይ)።

· የአላህን አንዳንድ ባህሪያት ለሌላ ቁሳቁስ ወይም ፍጡራን መሰየም (ለምሳሌ፥ ጣዖታት/የእድል ቁሶች)።

· አላህ ልጅ፣ እናት አልያም ሌላ ማንኛውም አይነት አጋር አለው ማለት።

በመሆኑም፥ የሰው ዘርን ወደ ክህደት መጎትጎት የሰይጣን ዋና ትኩረቱ ነው። ነገር ግን፥ ሰይጣን ሰዎችን ግልፅ የክህደት ተግባራትን እንዲፈፅሙ ማሳሳት ካልቻለ፥ እንደ ባዕድ አምልኮ፣ እድል መሳብ፣ አስትሮሎጂ እና ጥንቆላ የመሳሰሉ ይበልጥ ድብቅ የሆኑ መንገዶች ይጠቀማል። እንዲህ ያሉ እምነቶች በሁሉም ነገሮች ላይ ስልጣንና እውቀት ያለው አላህ ብቻ ከመሆኑ እና ጥቅምንም ሆነ ጉዳትን ማምጣት የሚችለው እርሱ ብቻ ከመሆኑ እውነታ ጋር ይጋጫሉ።

በሐይማኖት ላይ አዲስ ጭማሪ ማምጣት (ቢድዓ)

"...ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ፡፡..." ቁርዓን 5:3

ሰይጣን ሰውን እስልምና ውስጥ በአላህም ሆነ በነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ያልታዘዙ የተሳሳቱ እምነቶችን እና ተግባሮችን እንዲፈጥር አታሎ ያግባባል።

በመሰረቱ፥ እስልምና ያልተሟላ ወይም በአላህ ጎዶሎ ሆኖ የተገለጠ በመሆኑ አዳዲስ ፈጠራ (ቢድዓ) ያስፈልገዋል የሚለው እምነት በራሱ እንደ ክህደት (ኩፍር) ነው የሚታየው፤ ምክንያቱም አላህ ያወረደውን ነገር ማስወገድ ስለሚሆን።

ብዙ አዲስ ፈጠራዎች ልክ እንደ ሃይማኖታዊ ስራዓት በተመሳሳይ ልቅም ያለ ጥንቃቄ ይከናወናሉ፤ ብሎም ልክ አላህ እንደገለጠው ነገር ጠቃሚ ተደርገው ይታያሉ።

አደጋ ያለው እዚህ ላይ ነው፤ አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚከተሉ ሰዎች ስራዎቻቸው ተቀባይነት እንዳላቸው ያምናሉ፤ እውነታው ግን ሐጢዓት እየሰሩ ሆነው ሳሉ።

እነዚህ አዲስ ነገር ፈጣሪዎች መፀፀት እንዳለባቸው አይሰማቸውም፤ ጥፋታቸውን አያውቁትምና።

ግዳጅ (ፈርድ) ተግባራትን ችላ ማለት

"...ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና።..." ቁርዓን 29:45

ሰይጣን "… አላህን ከማውሳትና ከስግደትም ሊያግዳችሁ ብቻ ነው።..." [ቁርዓን 5:91] የሚፈልገው።

አላህ በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ የተወሰኑ ተግባራትን ግዳጅ (ፈረድ) አድርጓል፤ አምስቱ ዕላታዊ ሰላቶች እጅግ መደበኛ ከሆኑት ውስጥ ናቸው።

ስለዚህ፥ ሰይጣን የባሰ ወደ ሐጢዓት እንድንገባ እኛን በሰላታችን ላይ ቸልተኞች ለማድረግ ይፈልጋል።

ቀስ በቀስ ማታለል

ነቢዩ ሙሀመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የጣዖት አምልኮ እንዴት እንደተጀመረ፥ የሰይጣንን የቀስ በቀስና በትዕግስት የተመላ አቀራረብ በሚያሳይ መለኩ ገልፀውልናል።

በሆኑ ህዝቦች መሐል ይኖሩ የነበሩ አላህን ፈሪ ሰዎች በሞት በተለዩዋቸው ጊዜ ለክብራቸው የሚሆኑና ቅዱስነታቸውን የሚዘክሩ ሐውልቶችን እንዲያቆሙላቸው ወጣቶችን ሰይጣን አነሳሳቸው። ያ ትውልድ ካለፈና ህዝቡም በጊዜ ሂደት ሐውልቶቹ ለምን እንደቆሙ ከተዘነጋው በኋላ፥ ቀደምት አባቶቻቸው ያመልኳቸውና በዚያም አማካይነት ዝናብ ያዘንቡ እንደነበር ወደማመን ቀስ ብሎ አታለላቸው። ከዚያም ህዝቡ እነዚያን ሐውልቶች ማምለክ ጀመረ።

ይህን ቀስ በቀስ ማታለል በብዙ መንገዶች ይጠቀመዋል። ለምሳሌ፥ ሰይጣን ሰዎችን የተከለከሉ ፆታዊ ግንኙነቶችን ወደመፈፀም ሸውዶ ያስገባቸዋል፤ በመተያየት ይጀመራል፣ ወደሃሳብነት ያድጋል፣ ከዚያ ፈገግታ ወደመለዋወጥ፣ ቀጥሎ ንፁህ ወደሚመስል የሃሳብ ልውውጥ፣ ከዚያም ለብቻ ወደመገናኘት፣ በመጨረሻም ራሱን ወንጀሉን ወደመፈፀም ይገባል።

በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ሰዎች ፈርድ ሃይማኖታዊ ግዴታዎቻቸውን መስራት እንዲያቁሙ ለማድረግ በመፈለግ፥ ሰይጣን በመጀመሪያ የውዴታ የአምልኮ ተግባሮቻቸውን እንዲተው ያሳምናቸዋል፤ ይህ ደግሞ የግዴታዎቹም ላይ ሰነፍ ወደመሆን ይወስዳቸዋል።

በተጨማሪም፥ ቀለል ያሉ ወንጀሎችን ተራ እንደሆኑ ለማስመሰል ይሞክራል፤ ይህም በጊዜ ሂደት ወደ ትላልቅ ወንጀሎች ወደ መንሸራተት ይመራል።

ክፉ ሥራዎችን ማስዋብ

"... ይሠሩት የነበሩትንም ነገር ሰይጣን ለነሱ አሳመረላቸው፡፡" ቁርዓን 6:43

ሰይጣን ኃጢአቶችን ለሰዎች እንዲመቻቸው አድርጎ ያቀርባል፤ ልክ አደምና ሐዋን ከዛፉ ፍሬ እንዲበሉ እንዳታለላቸው አይነት።

ሰይጣን አደምን እንዲህ ሲል ሹክ አለው፥ "አደም ሆይ! በመዘውተሪያ ዛፍ በማይጠፋ ንግሥናም ላይ ላመላክትህን?" ቁርዓን 20:120

“’ጌታችሁም መልኣኮች እንዳትሆኑ ወይም ከዘላለም ነዋሪዎች እንዳትሆኑ እንጂ ከዚህች ዛፍ አልከለከላችሁም።... እኔ ለእናንተ በእርግጥ ከሚመክሩዋችሁ ነኝ።’ በማታለልም አዋረዳቸው፡፡ ከዛፊቱም በቀመሱ ጊዜ ... ጌታቸውም ‘ከዚህ ዛፍ አልከለከልኋችሁምን? ሰይጣንም ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነው አላልኳችሁምን?’ ሲል ጠራቸው፡፡” ቁርዓን 7:20-22

ምንም እንኳን አደም በብዙ የተፈቀዱ የምግብ አይነቶች ተከበው የነበሩ ቢሆንም፥ ሰይጣን ግን ከተከለከሉት ዛፍ እንዲበሉ ሊያሳምናቸው ችሎ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታም ሰይጣን ሰዎችን የተፈቀዱላቸውን ነገሮች ትተው ወዳልተፈቀዱላቸው ነገሮች እንዲሄዱ ያታልላቸዋል፤ ለምሳሌ ያህል፥ ከትዳር ይልቅ ወደ መማገጥ፣ ከቁርዓን ይልቅ ወደ ሙዚቃ፣ ከሐላል ገቢ ይልቅ ወደ ሐራም፣ እንዲሁም በስፋት ከሚገኙና ንፁህ ከሆኑ የተፈቀዱ ምግቦችና መጠጦች ይልቅ አነስተኛ መጠን ወዳላቸው ወደተከለከሉ ምግቦችና መጠጦች የመሄድ ነገር።

ስሜቶችን ማነሳሳት

"(የማይፈጸመውን) ተስፋ ይሰጣቸዋል። ያስመኛቸዋልም። ሰይጣንም ለማታለል እንጂ አይቀጥራቸውም።" ቁርዓን 4:120

ሁሉም ሰው ፍላጎቶችና ጉጉቶች አሉበት። ሰይጣን እነዚህን ስሜቶች በመነካካት የሰውን ልጅ፥ ድርጊቶች የሚያስከትሏቸውን መዘዞች ረስቶ፥ ያሻውን በመፈፀም ቅፅበታዊ ደስታን እንዲያገኝ ያሳምነዋል።

ይህ በዚህኛው ዓለም ህይወት አልያም በመጨረሻው የፍርድ ቀን ለፀፀትና ለውርደት መዳረጉ አይቀሬ ነው።

ጊዜን ማባከን

ሰይጣን ሰውን በኃጢዓት ማጥመድ ካልቻለ፥ ምንም ጥቅም በሌላቸው ረብ የለሽ ተግባራት ቢዚ እንዲሆን ያደርገዋል።

ጊዜያችንን በአግባቡ ከመጠቀም፣ ቀዳሚ ጉዳዮቻችንን ከመሙላት እና ከፍ ወዳሉ ግቦች ከመድረስ ይልቅ ሰይጣን ፋይዳ ቢስ በሆኑ ተግባራት እንድንጠመድ ያደርገናል።

ሰይጣንን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል

"ሰይጣን ለናንተ ጠላት ነው። ስለዚህ ጠላት አድርጋችሁ ያዙት።..." ቁርዓን 35:6

የመጀመሪያ እርምጃ ሰይጣን ጠላታችን መሆኑን ማወቅ ነው፤ ጠላትህን አስቀድመህ ካወቅከው፥ እሱን ማሸነፍ ትችላለህ።

የሰይጣን ጉልበት ያለው በዋናነት የማታለል ችሎታው ላይ ነው፤ ስለዚህ ራሳችንን በተሻለ መልኩ ለመጠበቅ፥ የብልጣ ብልጥ ዘዴዎቹንና አካሄዶቹን መረዳት ይኖርብናል።

እርዳታን ከአላህ ዘንድ ፈልጉ

አላህን ጥበቃውን መለመንና እርዳታን ከእርሱ ብቻ መፈለግ ሰይጣንን ማሸነፊያ አንድ መሳሪያ ነው።

የተፍለቅላቂው (ሱራህ አል ፈለቅ) እና የሰው (ሱራህ አል ናስ) የቁርዓን ምዕራፎች በመደበኛነት ከሰይጣን ለመጠበቅ ሊውሉ ስለሚችሉ እነሱን መቅራት ይኖርብናል።

በሕይወት እስካለን ድረስ ሰይጣን እኛን ለማሳሳት ከመሞከር መቼም ራሳችንን በተጠንቀቅ ልንጠብቅና እንደማያቆም ልብ ልንል ይገባል።

ምህረትን ፈልጉ

ነቢዩ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፥ "ያ ከኃጢዓት የሚጸጸት ሰው ኃጢዓት እንደሌለበት አይነት ነው።" ኢብን ማጃህ

ለሰይጣን ሴራዎች ተሸናፊ ከሆንንም እንኳ፥ አላህ በጸጋውና በእዝነቱ ይሁንበት፥ ጥፋተኝነታችንን በማመንና ወደአላህ በመፀፀት አሁንም ስህተቶቻችንን የማረም እድሉ አለን።

ነቢዩ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፥ "ሰይጣን የልቅናውን ጌታ እንዲህ አለው፥ ‘ጌታ ሆይ፥ በልቅናህ ይሁንብኝ፥ነፍሶቻቸው በስጋዎቻቸው እስካሉ ድረስ ባሪያዎችህን መንገድ ለማሳት መሞከሬን እቀጥላለሁ።’ ጌታም እንዲህ አለ፥ ‘በልቅናዬ እና በግርማዬ እምላለሁ፥ ይቅርታዬን እስከጠየቁ ድረስ እነርሱን ይቅር ማለቴን እቀጥላለሁ።’” አህመድ

ተውበት (ፀፀት) ተቀባይነት እንዲያገኝ፥ ከልብ የመነጨ መሆንና ያንን ወንጀል መቼም ደግሞ ላለመፈፀም መቁረጥ ግዴታ ነው።

ከኃጢዓት አካባቢዎች ይራቁ

አላህ አዳምን አንድን የተለየ ዛፍ በከለከለው ጊዜ፥ ያዘዘው "ከዚህ ዛፍ እንዳትበላ" ብሎ ሳይሆን "ወደዚህ ዛፍ እንዳትቀርብ" በማለት ነበር። ቁርዓን 2:35።

ስለዚህ እኛም ኃጢዓት ወደመስራት ሊወስድ ከሚችል ማንኛውም ነገር ራሳችንን ማራቅ አለብን።

መልካሞችን ይወዳጁ

የአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ይህን መክረዋል፥ "ሰው በቅርብ ባልንጀራው መንገድ ላይ ነው፤ ስለዚህ የምትወዳጁትን በጥንቃቄ ምረጡ።" ቲርሚዚ

የሚወዳጇቸው ሰዎች ውሳኔዎችዎ እና ተግባሮችዎ ላይ ከባድ ተፅዕኖዎች ይኖሯቸዋል። መልካም ባልንጀሮች ስለአላህ ያስታውሱዎታል ብሎም መልካምን እንዲሰሩ ያበረታቱዎታል፤ መጥፎ ባልንጀራ ግን ወደ ሰይጣን እቅፍ ይመራዎታል።

በጎ ሥራዎችን ይስሩ

በሃይማኖታዊ ተግባራት መጠመድ፥ በተለይም በሰላት፥ ሰይጣንን ማሸነፊያ እጅግ በጣም ጥሩ መንገድ ነው።

ሰዎች ጊዜያቸውን ለመልካም ካዋሉ፥ በሰይጣን ማታለያዎች ተፅዕኖ ላይ የመውደቅ እድላቸው አነስተኛ ነው የሚሆነው።

"ከሰይጣንም (በኩል) ጉትጎታ ቢያገኝህ በአላህ ተጠበቅ፡፡ እርሱ ሰሚው ዐዋቂው ነውና፡፡" (ቁርዓን 7:200)

ማጠቃለያ

ሰይጣን ጋር ያለብን ፍልሚያ ስለወጥመዶቹ ከተረዳን እና እሱን የማሸነፊያ ብልሃቶቹን ከተገበርን ብቻ ነው በድል ሊጠናቀቅ የሚችለው።

በመጨረሻው የፍርድ ቀን፥ ሰይጣን ወንጀሎቹን እና ተንኮሎቹን ይናዘዛል።

ከመላ ፍጥረተ አለም ፊት ቆሞ እውነት ተናጋሪው አላህ እንደሆነ እና እርሱ (ሰይጣን) ግን ውሸታም መሆኑን ያውጃል።

ወንጀሎቻችንን ይቅር እንዲለን እና ከሰይጣን ወጥመዶች ጥበቃ እንዲያደርግልን ኃያሉን አላህ፥ እጅግ ውብ በሆኑ ስሞቹ እና በረቂቅ ባህሪዎቹ ይሁንበትና፥ እንለምነዋለን።

Similar Downloads

No related download found!