Description
የሪባ (ወለድ፣ አራጣ) አደጋዎች
"እናንተ በአላህ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! አራጣን የተነባበሩ እጥፎች ሲሆኑ አትብሉ። ከገሀነም እሳት ትድኑም ዘንድ አራጣን በመተው አላህን ፍሩ።" ቁርዓን 3፡130
መሰረታዊያኑን ይማሩ
መግቢያ
አንድ ሙስሊም ሐራም በመሆኑ ምክንያት የአሳማ ስጋ ፈፅሞ አለመብላቱ፤ ሐራም በመሆኑ ምክንያት እናቱን አልያም እህቱን ፈፅሞ አለማግባቱ፤ ሆኖም ይኸው ተመሳሳይ ሰው ሪባ (ለምሳሌ፥ ወለድ፣ አራጣ) መብላት ላይ ግን ምንም ችግር የሌለበት መሆኑ አያስደንቅም?
ሪባ ውስጥ መግባት ወደጀሐነም ሊወስድ የሚችል አብይ ሐጢዓት መሆኑን ግን ያውቃሉን?
“…አራጣን ወደ መብላት የተመለሱ ሰዎች እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው። እነርሱ በውስጧ ዘወታሪዎች ናቸው።” ቁርዓን 2፡275
ሪባ ጋር መነካካት ይህን ያህል ለቅጣት የሚዳርግ ከሆነ፥ ለምንድነው ብዙ ሙስሊሞች ወደዚህ ሐጢዓት የሚገቡት እና ጉዳዩን አቅልለው የሚያዩት?
የሪባ ፍች
ሪባ፥ “መጨመር”፣ “ማደግ” እና “መብለጥ” የሚሉ ፍችዎች ካሉት ራባ ከሚል ግስ የተመሰረተ የአረቢኛ ስም ነው።
ለተቀማጭ ገንዘብ በባንኮች የሚከፈልን አልያም እንደ መኪና፣ መኖሪያ ቤት መግዣ ወይም ክሬዲት ካርድ በመሳሰሉ ብድሮች ላይ የሚታሰብን ወለድ ያካትታል።
ሪባ ሐራም ለመሆኑ ማስረጃ
ሪባ ሐራም እና በእስልምና እጅግ ከባድ ከሆኑት ሐጢዓቶች መካከል አንዱ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።
በአላህና በቁርዓን ላይ እውነተኛ እምነት ላላቸው፥ ሪባን የሚከለክለው ይህ ግልጽ አንቀጽ በቂያቸው ነው፤
"…አላህ ግን መሸጥን ፈቅዷል። አራጣን እርም አድርጓል።" ቁርዓን 2፡275
በቁርዓን ውስጥ፥ አላህ በማንም ላይ ጦርነትን አያውጅም፥ በሪባ ከሚጠቃቀሙቱ ላይ በስተቀር።
"እናንተ በአላህ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! አላህን ፍሩ። በእንጥልጥል ላይ ያሉ (ያልተሰበሰቡ) የወለድ ክፍያዎችን አትውሰዱ። ትክክለኛ አማኞች
ከሆናችሁ (ተጠንቀቁ)።
የታዘዛችሁትን ባትሰሩ ከአላህና ከመልዕክተኛው ጦርነት ታውጆባችኋል።" ቁርዓን 2፡278-279
አላህ፥ ኃያሉ አምላክ፥ ሪባ ሐራም መሆኑን በሰፊው ግልፅ ካደረገ በኋላ በእርስዎ ላይ ጦርነት እንዲያውጅብዎ ይሻሉን?
ነቢዩ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሪባን መብላት ለጀሃነም ከሚዳርጉ ሰባቱ ኃጢአቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን አስጠንቅቀዋል። (ቡኻሪ እና ሙስሊም)
ሪባ በየትኛውም መልኩ ሐራም ነው፤ ነቢዩ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዳሉት (ሙስሊም):
"ሪባ የሚበላን፣ ሪባ የሚሰጥን፣ ምስክር የሚሆንን፣ እንዲሁም የሪባ ልውውጥ ውል የሚፅፍን አላህ ረግሞታል።”
ከነዚያ አላህ ከረገማቸው ሰዎች መሐል አይሁኑ!
ሪባ ለምን ሐራም ሆነ?
ለሪባ ሐራም መሆን የመጀመሪያውና ቀዳሚው ምክንያት የአላህ አዋጅ ስለሆነ ነው።
ወሰን የለሽ ጥበበኛነቱ ላይ ተመስርቶ ነው አላህ አንድን ድርጊት ፈርድ ወይም ሐራም የሚያደርገው፥ ለሰው ልጅ ለዱኒያም በአኼራም የሚበጁትን ነገሮች የሚያዘው፤ አላህ እጅግ ጠበበኛና ሁሉን አዋቂ ነውና።
ሪባ ለምን ሐራም እንደሆነ የእስላም ሊቃውንት የሚከተሉትን ምክንያቶች ጠቅሰዋል፦
• ብዙ ሀገራት፥ ትላልቅና ትናንሽ፥ የተዘፈቁባቸው የውጪ እዳዎች በጣም ከፍተኛ ከመሆናቸው የተነሳ የብድሮቹ የወለድ ክፍያዎች በመላ ሀገራቱ ላይ አድቃቂ ሸክሞች ናቸው።
ዕዳ ገዳይ ነው። በዓለም ዙሪያ በየአመቱ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ህፃናት በድህነትና በዕዳ ሁኔታዎች ምክንያት ይሞታሉ።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ፥ ናይጄሪያ ስላለባት ዕዳ አስተያየት ሲሰጡ፦
"እስከ 1985 ወይም 1986 ድረስ አጠቃላይ የተበደርነው ገንዘብ $5 ቢሊዮን አካባቢ ነበር፤ እስካሁን ወደ $16 ቢሊዮን ከፍለናል፤ ሆኖም ግን ገና ከ$28 ቢሊዮን በላይ እንደሚቀርብን እየተነገረን ይገኛል።
ያ $28 ቢሊዮን የመጣው በውጭ ክሬዲተሮች (አበዳሪዎች) ኢፍትሐዊ የወለድ ስሌት መጠኖች ምክንያት ነው።
በዚህ ዓለም ውስጥ እጅግ አስከፊ ነገር ምንድነው ካላችሁኝ፥ ጥምር ወለድ ነው ባይ ነኝ።" - እዮቤልዩ 2000 ዜና ጥንቅር፣ ነሐሴ 2000
• ሪባ ከወንድማማችነት እና ከመተዛዘን መንፈስ ጋር ይጣረሳል፤ እናም በስግብግብነት፣ ራስ ወዳድነት እና ልበ ደረቅነት ላይ የተመሰረተ ነው።
• ሪባ ለዋጋ ግሽበት (ኢንፍሌሽን) አብይ አስተዋፅዖ ከሚያደርጉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው።
• ሪባ በዕዳዎች መቆለል የተነሳ ቀውስ እና ዝቅጠትን ያስከትላል።
• ሪባ ምንም የኪሳራ አደጋ የሌለበት የተረጋገጠ ትርፍ ነው፤ ስለሆነም፥ ሁለቱም አካላት አደጋንም ትርፍንም በእኩል ከመጋራት ይልቅ ሁሉንም አደጋ ተበዳሪ ብቻውን ይሸከማል።
• ሪባ በማህበረሰብ ውስጥ፥ ሀብታሞች ለባለፀጋነታቸው የሚሸለሙበትን ያልታደሉቱ ደግሞ ተጨማሪ ለመክፈል የሚገደዱበትን፥ ሞኖፖሊ ይፈጥራል!
በ2008ቱ እና 2009ኙ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ቀውስ በመኖሩ፣ የቫቲካን ዕለታዊ ጋዜጣ የሆነው ለ’ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ ቫቲካን ኢስላማዊው የፋይናንስ ስርዓት ምዕራባዊያን ባንኮችን በቀውሱ ላይ በአማራጭነት ሊያግቸው እንደሚችል መናገሯን ዘግቧል።
"ኢስላማዊ ፋይናንስ የተመሰረተባቸው ስነምግባራዊ መርሆዎች ባንኮችን ከደምበኞቻቸው እና እያንዳንዱ የፋይናንስ አገልግሎት ተለይቶ ሊታወቅበት ከሚገባው እውነተኛ መንፈስ ጋር ሊያቀራርቡ ይችላሉ።” ስትል ቫቲካን መክራለች።
ሪባን መሰረት ያደረገ ገበያ በሚወድቅበት፥ ኢስላማዊ የፋይናንስ ተቋማት ተመሳሳይ ዕጣ አይገጥማቸውም ምክንያቱም አደጋን ሁለቱም ወገኖች በእኩል ስለሚጋሩ።
ተበዳሪው ዋናውን ብድር መመለስ የማይችል ከሆነ አበዳሪዎችም የገንዘብ ኪሳራ አደጋውን በከፊል ስለሚጋሩ ሲያበድሩ በይበልጥ ይጠነቀቃሉ።
ሪባ ይህን ሁሉ ችግር እንደሚፈጥር ከግምት ሲገባ፥ እስልምና እንዲህ ያለውን ፀያፍ ተግባር መከልከሉ አይደንቅም።
ከሪባ እንዴት መራቅ እችላለሁ?
በካፒታሊስት ማህበረሰብ ውስጥ መኖር ሙሉ በሙሉ ከሪባ መራቅን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ነገር ግን፥ ይህ በጉዳዩ ላይ እንደፈለጉ በነፃነት ለመጨመላለቅ ሠበብ መደረግ የለበትም።
ከዚህ እርኩስ ነገር ርቆ የመቆያ አንድ ግልፅ መንገድ፥ ሪባ ያለው ብድር ውስጥ አለመግባት ነው።
ሌሎች መፍትሄዎች የሚከተሉትን ይጨምራል፦
• ከወለድ ነፃ የባንክ አካውንቶችን መክፈት።
• የወለድ ቅጣት ያለባቸው ኮንትራቶች ውስጥ አለመግባት፤ ኒያው በጊዜ ከፍሎ ማጠናቀቅ ቢሆንም እንኳ።
• ቀነ ገደብ በማሳለፍ ለቅጣት ላለመዳረግ ክፍያዎችን በጊዜ መፈፀም።
• ሪባን ውስጥ ሳይገቡ ንግድን ለመቀጠል የሚያስችሉ ደንብና ግዴታዎች ካሉ ማሟላት።
• ሁኔታዎች ሲፈቅዱ የገንዘብ ብድርን ከቤተዘመድ አልያም ከጓደኞች መውሰድ።
• ለኢስላማዊ አሰራር ተገዢ ከሆኑ ባንኮች ጋር መስራት።
• መኖሪያ ቤት ያለሪባ መግዛት ካልቻሉ መከራየት።
• "ጤናማ ብድር" (አል-ቀርድ አል-ሐሰና)፥ አንዱ ለሌላው መልካምን በማሰብ የሚያቀርበው ሪባ የሌለበት ብድር፥ መውሰድ/ማዘጋጀት።
ባንክ የሚሰጥዎትን ወለድ በተመለከተ፥ ለባንኩም አይመልሱት ለራስዎም አያውሉት። ይልቁንም፥ ለበጎ አድራጎት ተግባር ያውሉት፥ ለምሳሌ ለድሆች መስጠት፣ ለኢስላማዊ ማዕከላትና ለመስጂዶች አላቂ እቃዎችን (እንደ መፀዳጃ ቤት ወረቀቶች ያሉ) መግዛት፣ እና ባለዕዳዎችን መርዳት።
ነገር ግን፥ ለዚህ አጂርን አይጠብቁ።
ከሪባ ለመራቅ እና የትኞቹ ልውውጦች የተፈቀዱ እንደሆኑ ለመወሰን እጅግ አስተማማኙ መንገድ የእስልምና ምሁራንን ማማከርና በእውቀታቸው መጠቀም ነው።
ምንም ማድረግ ካልቻልኩስ?
በእስልምና፥ አንድ ሰው በችግር ወቅት ለፈፀመው የተከለከለ ተግባር ማርታን ያገኛል።
ስለዚህ፥ አንድ ሰው ሪባን እንዲጠቀም ቢገደድና ያን ካላደረገ ለከፋ ችግር አልያም ለሞት የሚዳረግ ከሆነ የአደጋው ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ በጊዜያዊነት ይፈቀዳል።
ከሪባ በመቆጠቡ ምክንያት የሚደርስበትን ችግር ለአላህ ብሎ የተጋፈጠ ምንዳን እንደሚያገኝ ግን ልብ ይበሉ።
ስለሰውዬው ግላዊ ሁኔታ ግንዛቤው ያለውና በእስልምና እውቀት የታነፀ ሰው ነው በእርግጥም ሰውዬው ችግር ውስጥ መሆን አለመሆኑን መወሰን ያለበት።
አለበለዚያ፥ ይህን የህጉን የተለየ ከለላ ተንተርሰው ብዙ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሪባን ወደመጠቀም ሊገቡና አላህ ላዘጋጃቸው ቅጣቶች ሊዳረጉ ይችላሉ።
ሪባን በመጠቀም የመጀመሪያ ቤትን ከመግዛት ጋር በተያያዘ በሙስሊሞች ዘንድ አንድ የተለመደ የተሳሳተ አረዳድ አለ።
አንዳንድ ሰዎች “መሰረታዊ ፍላጎት” ስለሆነ እንደሚፈቀድ ያውጃሉ።
አንድ ሰው ቤት ከመግዛት ይልቅ መከራየት የመቻሉ እውነታ ይህን ውድቅ ያደርገዋል።
ይህ ንድፈ ሃሳብ እውነትነት ቢኖረው፥ ውሃ ማግኘት እየተቻለም ቢሆን የመጀመሪያውን የአልኮል ጠርሙስ መውሰድ ይፈቀዳል እንደማለት አይሆንምን?
አልያም የተፈቀደ አማራጭ እያለ የአሳማ ስጋ መብላት?
ሌሎችን አታሎ ይህን ለማሳመን የቱንም ያህል ቀላል ሊሆን ቢችልም፥ ይህን ማስታወስ ግን አለብን፦
"...አላህ የምትገልጹትን ነገርም ሆነ የምትደብቁትን ሁሉ ያውቃል።" ቁርዓን 5:99
ራስንና ሆነ ቤተሰብን ለማስተዳደር ኪራይ መክፈል “ገንዘብ ማባከን” አይደለም።
ኢንሻአላህ፥ ሁሉን አድናቂው አላህ፥ ይህን እንደሰደቃ ቆጥሮለት ምንዳን ይሸልመዋል፦
"አንድ ሰው ከአላህ ምንዳን ፈልጎ ቤተሰቦቹ ላይ ሲሳይን ካወጣ፥ እንደሰደቃ ይቆጠርለታል። (ቡኻሪ እና ሙስሊም)
ስኬት በዚህኛውም በወዲያኛውም ሕይወት
ይህን የሪባ ጉዳይ በምንመረምር ጊዜ፥ እውነተኛ ስኬት በአላህ እርዳታ ብቻ እንደሚገኝ ማስታወስ ይኖርብናል።
ሐላል በሆነው መንገድ ከኖርንና ሐራም ከሆነው ከራቅን፥ ሐብታችን በዚህኛውም በወዲያኛውም አለም የተባረከና የሚጠቅም ይሆናል።
በውስጡ ምንም በረካ ከሌለበት እና የስቃይ ምንጭ እንዲሆን ከተረገመ፥ በሪባ የተገኘ ትርፍ ገንዝብ ምን ሊበጅ?
በቂያም ቀን፥ ሰዎች ከመቃብሮቻቸው ፈጥነው ይነሳሉ - በሪባ ተግባር ላይ ተጠምደው ከነበሩት በስተቀር።
እነርሱ ይቆሙ እና ከዚያም አውድቅ እንዳለበት ሰው ይንፈራፈራሉ፤ ምክንያቱም፦
"እነዚያ አራጣን የሚበሉ ሁሉ ያ ሰይጣን ሰፍኖበት ራሱን የሚስት ሰው ከአውድቅቱ እንደሚነሳ አይነት ሁነው እንጂ (ከመቃብራቸው) አይነሱም።
ይህም የሆነው እነርሱ መሸጥ ልክ እንደ አራጣ ነው በማለታቸው ነው። አላህ ግን መሸጥን ፈቅዷል። አራጣን እርም አድርጓል።" ቁርዓን 2:275
እነዚያ ሪባ የሚበሉና ከልብ ተፀፅተው ከዚህ ታላቅ ሐጢዓት የማይመለሱ የሚጠብቃቸው ቅጣት እንዲህ ያለ ነው።
እነዚያ የአላህን ደስታ በመፈለግ ለስኬት የሚተጉ፥ ከሚከተለው አንቀፅ መፅናናትን ያገኛሉ፦
"እናንተ በአላህ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! አራጣን የተነባበሩ እጥፎች ሲሆኑ አትብሉ። ከገሀነም እሳት ትድኑም ዘንድ አራጣን በመተው አላህን ፍሩ።" ቁርዓን 3:130
በተጨማሪም በወዲያኛው አለም እንዴት ስኬታማ መሆን እንደምንችል ቀርቦልናል፦
"የምዕምናን ቃል ግን የነበረው ወደ አላህና ወደ መልዕክተኛው በመካከላቸው ሊፈርድ በተጠሩ ጊዜ ‘ሰማን ታዘዝንም’ ማለት ብቻ ነው።
እነዚህ ማለት እነርሱ የፈለጉትን የሚያገኙ ናቸው።" ቁርዓን 24:51
ማጠቃለያ
ሪባ ሐራም እና አብይ ሐጢዓት እንደሆነ ማንም ሊጠራጠር አይችልም፤ እንዲሁም ምንም አይነት አላህን አልታዘዝም ባይነት ለእርሱ ቅጣት የመጋለጥ አደጋን አይመጥንም።
የዚህ ዓለም ሕይወት አጭርና ወረተኛ መሆኗን፥ እንዲሁም በህይወት የመኖራችን አላማ ውበትንና ሐብትን ማሳደድ ሳይሆን አላህን በትክክል መገዛት እና በእሱ ህግጋት እየተመራን መኖር እንደሆነ ማስታወስ አለብን።
ሪባ ስለተንሰራፋ እና ስለተለመደ ብቻ፥ የተፈቀደ ተግባር አያደርገውም።
"አላህንም የሚፈራ ሰው ለእርሱ መውጫን ያደርግለታል። ከማያስበውም በኩል ሲሳይን ይሰጠዋል፤ በአላህም ላይ የሚጠጋ ሰው እርሱ በቂው ነው። " ቁርዓን 65:2-3
