Description
ለሰው ዘር የወረደ የመጨረሻው መለኮታዊ ርዕይ
ቁርዓን ምንድን ነው?
የአላህ ቃል
ቁርዓን፥ ለነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በመልዕክተኛው ጂብሪል አማካይነት የተወረደ የኃያሉ አምላክ (በአረቢኛ አላህ) ቀጥተኛ ንግግር ነው።
"የመጽሐፉ መወረድ አሸናፊው ጥበበኛው ከሆነው አላህ ነው።" - ቁርዓን 39፡1
የሰው ልጆች መመሪያ
ቁርዓን "ለሰዎች መሪ ... ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) መለያ ..." [ቁርዓን 2፡185] ነው።
ለሰው ልጅ እውነትን ከሐሰት ለመዳኘት የሚረዳው ጥቆማ ያቀርባል፤ ያለሱ የሰው ልጅ በእርግጥም ጠፊ ነበር።
የመጨረሻው ርዕይ
ቁርዓን በኃያሉ አላህ (አምላክ) የተወረደ የመጨረሻው መለኮታዊ መፅሐፍ ሲሆን በቀደሙ መፃህፍት ክፍሎች የቀረውን እንጥፍጣፊ እውነት ያረጋግጣል፤ እንዲሁም በእኒህን መሰል መፃህፍት የአሁን ዘመን ቅጂዎች ውስጥ ሰርገው የገቡ የፈጠራ ታሪኮችንና ጭማሪዎችን ያስተባብላል ብሎም ያርማል።
"እናንተ መጽሐፉን የተሰጣችሁ ሆይ! . . . ከእናንተ ጋር ያለውን የሚያረጋግጥ ሆኖ ባወረድነው (ቁርዓን) እመኑ፡፡" - ቁርዓን 4፡47
ቁርዓን የተወረደው እንዴት ነው?
ቁርዓን ለነብዩ ሙሀመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የተወረደው እና ተጠብቆ ያለው በተወረደበት በአረብኛ ቋንቋ ብቻ ነው። ነገር ግን፥የቁርዓን ፍች ትርጉሙ በብዙ ቋንቋዎች ይገኛል።
ቁርዓን በአንድ ርዕይ አልነበረም ሙሉው መፅሐፍ የተወረደው፤ ይልቅስ ርዕዩ 23 ዓመታትን ፈጅቷል።
ለዚህም ሲባል፥ ስለ ቁርዓን ተገቢውን ግንዛቤ ለመጨበጥ አንቀፆቹ በምን በምን ሰበቦች እንደወረዱ ማወቅ ወሳኝ ነው፤ ካልሆነ አስተምህሮቶቹ በተሳሳተ መንገድ ሊወሰዱ ይችላሉ።
ከአላህ ስለመሆኑ እንዴት ማወቅ እችላለሁ?
ተጠብቆ መቆየት
ለተራዘመ ጊዜ በስራ ላይ ሲዘዋወር የቆየ ግን ደግሞ ልክ መጀመሪያ ሲወረድ እንደነበረው ንፅህናው ተጠብቆ ያለ ሐይማኖታዊ ቅዱስ መፅሐፍ ቁርዓን ብቻ ነው። ከተወረደበት ከ1400 ዓመታት በላይ ጀምሮ ምንም ነገር አልተጨመረበትም፣ አልተቀነሰበትም አልያም አልተለወጠበትም።
"እኛ ቁርዓንን እኛው አወረድነው። እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን።" - ቁርዓን 15፡09
ቁርዓን ተጠብቆ የሚኖረው በፅሁፍ ብቻ ሳይሆን በወንዶች፣ በልጆች እና በሴቶች ልቦችም ውስጥ ነው። ዛሬ፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቁርዓንን ከሽፋን እስከ ሽፋን በቃል ሃፍዘውታል።
ሳይንሳዊ ተዓምራት
ቁርዓን ዘመናዊ ሳይንስን አይፃረርም፥ ይደግፈዋል እንጂ።
ስለቁርዓን እጅግ አስደናቂ ከሆኑ ገፅታዎች ውስጥ አንዱ እንደ ኢምብሪዮሎጂ፣ ሜትሮሎጂ፣ አስትሮኖሚ፣ ጂኦሎጂ እና ኦሺኖሎጂ በመሳሰሉ ልዩ ልዩ የጥናት መስኮች ውስጥ የሚገኙ ተፈጥሯዊ ክስተቶችን በትክክል የሚገልፁ በርካታ አንቀፆች መያዙ ነው።
ተመራማሪዎች ወደኋላ ከ7ኛው መቶ ክ/ዘመን ለሆነ መፅሃፍ ገለፃዎቹን እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ ትክክለኛ ሆነው አግኝተዋቸዋል።
"እርሱም (ቁርዓን) እውነት መሆኑ ለእነርሱ እስከሚገለፅላቸው ድረስ በአጽናፎቹ ውስጥና በነፍሶቻቸውም ውስጥ ያሉትን ተዓምራቶቻችንን በእርግጥ እናሳያቸዋለን።" - ቁርዓን 41፡53
በእርግጥ፥ በቁርአን ውስጥ የተጠቀሱት ብዙዎቹ ሳይንሳዊ ተአምራት በቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ዘመናዊ እድገት ምክንያት ገና በቅርቡ ነው ሊታወቁ የቻሉት።
ቀጣዮቹን ይመልከቱ፡
• ቁርዓን ስለሰው ልጅ ፅንስ እድገት ዝርዝር ገለፃ ይሰጣል። እነዚህ ዝርዝሮች በሳይሳዊው ማህበረሰብ ዘንድ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ የማይታወቁ ነበሩ።
• ቁርዓን የህዋ አካላት (ከዋክብት፣ ፕላኔቶች፣ ጨረቃዎች፣ ወዘተ.) ሁሉም ከአቧራ ደመናዎች እደተሰሩ ይገልፃል። ከዚህ በፊት ባይታወቅም፥ አሁን ላይ ይህ እውነታ የዘመናዊ ኮስሞሎጂ የማይሻር መርህ ሆኗል።
• ሁለት ባህሮች የየራሳቸውን ሙቀት፣ እፍግታ እና የጨዋማነት መጠን እንዳስጠበቁ መገናኘት የሚያስችላቸው መከለያ መኖሩን ዘመናዊ ሳይንስ ደርሶበታል።
እነዚህ የአላህ ምልክቶች በቁርዓን ውስጥ ከ1400 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በግልጽ ተጠቅሰዋል።
ብጤ የለሽ መሆን
ከተወረደበት ጊዜ ጀምሮ፥ በውበቱ፣ በርትዑ፣ በግርማው፣ በጥበቡ፣ በትንቢቶቹ እና በሌሎች ምሉዕ ባህሪያቱ የቁርዓንን የሚመስል አንድ ምዕራፍ ሊያፈልቅ የቻለ አንድም ሰው የለም።
"በባሪያችንም ላይ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆኑ ከብጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ። እውነተኞችም እንደሆናችሁ ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ።" - ቁርዓን 2፡23
ነቢዩ ሙሐመድን (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አንቀበልም ያሉት ሰዎች፥ ምንም እንኳ በቁርዓን ቋንቋ እጅግ ሲበዛ አንደበተ ርቱዕ የነበሩ ቢሆኑም፥ ይህ ፈተና አልተሳካላቸው። ፈተናው እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ምላሽ ሳያገኝ አለ።
ከመጣረሶች የፀዳ
ሰዎች በሚፅፉ ጊዜ፥ እንደ ፊደልና ሰዋስዋዊ ስህተቶች፣ የሚጋጩ ሃሳቦች፣ የተዛቡ እውነታዎች፣ የመረጃ መዝለል እና ሌሎች ልዩ ልዩ ግድፈቶችን መስራታቸው አይቀሬ ነው።
"ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር።" - ቁርአን 4፡82
ቁርዓን ምንም አይነት መጣረሶች በውስጡ የሉበትም፥ በውሃ ዑደት ሳይንሳዊ ማብራሪያዎች፣ በኢምብሪዮሎጂ፣ በጂኦሎጂ እና ኮስሞሎጂ ዙሪያ ይባል በታሪካዊ እውነታዎችና ሁነቶች አልያም በትንቢቶች ረገድ።
የነብዩ ሙሐመድ የፈጠራ ድርሰት ሊሆን አይችልም ነበርን?
ነቢዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መሐይም የነበሩ ስለመሆናቸው በታሪክ የሚታወቅ ሐቅ ነው፤ እርሳቸው ማንበብም ሆነ መፃፍ የማይችሉ ነበሩ።
በቁርዓን ውስጥ ከሚገኙ ሳይንሳዊ እና ታሪካዊ ትክክለኛነታቸው ከሰመሩ ጉዳዮችም ጋር ሆነ ከዚህ አስደማሚ መፅሐፍ ስነፅሁፋዊ ውበት ጋር ግንኙነት ሊኖረው በሚችል አንድም የሙያ መስክ ስልጠና አልወሰዱም።
በቁርዓን ውስጥ ስለቀደሙ ሕዝቦች እና ስልጣኔዎች የተነገሩ ታሪኮች የላቀ ትክክለኛነት በማንኛውም አይነት ሰው የተፃፉ ናቸው ለማለት የሚታሰብም አይደል።
"ይህም ቁርዓን ከአላህ ሌላ (ከሆነ ፍጡር) የተቀጠፈ ሊሆን አይገባውም።" - ቁርዓን 10፡37
የመለኮታዊ ርዕይ ዓላማ
በአንድ እውነተኛ አምላክ ለማመን
"አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም። (እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው።" - ቁርዓን 2፡163
በመላው ቁርዓን የተወሳ ከሁሉም ይበልጥ እጅግ አንገብጋቢ ርዕሰ ጉዳይ በአንድ እውነተኛ አምላክ ማመን ነው።
እሱ አጋር እንደሌለው፣ ልጅ እንደሌለው፣ ብጤ እንደሌለው፣ እንዲሁም ከእርሱ በስተቀር የመመለክ ስልጣን ያለው ሌላ ምንም አካል እንደሌለ አላህ ይነግረናል።
ከአላህ ጋር ሊነፃፀር የሚችል ምንም ነገር የለም ብሎም አንድም የእርሱ ፍጥረት እርሱን አይመስልም።
ቁርዓንም ሰዋዊ ባህሪያትን እና ውስንነቶችን ለአላህ የመስጠትን አካሄድ አይቀበልም።
ሁሉንም ሐሰተኛ አማልክት ለመጣል
"ሰዎች ሆይ፣ አላህን ተገዙ። በእርሱ ምንም አታጋሩ።" - ቁርዓን 4፡36
መመለክ የተገባው አንድዬ አላህ ብቻ በመሆኑ፥ ሐሰተኛ ጣኦታትና ሐሰተኛ አማልክት ወዲያ ሊጣሉ ይገባል።
ቁርዓን በተጨማሪም መለኮታዊ ባህሪያትን ከአላህ ሌላ ለማንም ሆነ ለምንም የመስጠት አካሔድን አይቀበልም።
የቀድሞ ዘመን ታሪኮችን ለመተረክ
ቁርዓን እንደአደም፣ ኑኅ፣ ኢብራሂም፣ ኢሳና ሙሳ የመሳሰሉ ቀደምት ነቢያት እውነተኛ ታሪኮችን ጨምሮ ጠቃሚ ትምህርት ያላቸው በርካታ ተረኮችን በውስጡ ይዟል።
ስለነዚህ ታሪኮች አላህ እንዲህ ይላል፥
"በታሪካቸው ውስጥ ለአዕምሮ ባለቤቶች ሁሉ በእርግጥ መገሰጫ ነበረ።" - ቁርዓን 12፡111
ስለፍርዱ ቀን እኛን ለማሳሰብ
እያንዳንዱ ሰው ሞትን እንደሚቀምስ እና ለሁሉም ድርጊቶቹና ንግግሮቹ ተይዞ እንደሚጠየቅ ይህ የተከበረ መጽሐፍ ያሳስበናል፤
"በትንሣኤም ቀን ትክክለኛ ሚዛኖችን እናቆማለን። ማንኛይቱም ነፍስ ምንንም አትበደልም። ..." - ቁርዓን 21፡47
የሚፈለገውን የሕይወት መንገድ ለመከተል
ከምንም በላይ፥ የህይወት ዓላማ አላህን በብቸኝነት መገዛት፥ እና ህይወትን በእሱ በታዘዘው የህይወት መንገድ መሰረት መምራት መሆኑን ቁርዓን ያስተምራል።
በእስልምና አምልኮ አላህ የሚወዳቸውንና የሚደሰትባቸውን ሁሉንም ተግባራትና ንግግሮች (የግልም ሆኑ የአደባባይ) የሚያካትት አጠቃላይ ቃል ነው።
ስለዚህ፥ አላህ የሚያዝዘውን በመፈጸም፥ አንድ ሙስሊም አላህን ያመልካል ብሎም የሕይወት አላማውን ይሞላል።
የሚከተሉት ከቁርዓን የወጡ የአምልኮ ምሳሌዎች ናቸው፡
ሰላት መስገድ፤
"እናንተ በአላህ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ፥ ከአላህ ቁጣ ትድኑ ዘንድ በስግደታችሁ አጎንብሱ። በግንባራችሁም ላይ ተደፉ (ሩኩዕና ሱጁድ አድርጉ) ጌታችሁንም በትክክል ተገዙት። በጎንም ነገር ስሩ ልትድኑ ይከጀልላችኋልና። " - ቁርዓን 22፡77
ምፅዋት መስጠት፤
"... ለግሱም፤ ለነፍሶቻችሁ መልካምን ይሰጣችኋልና። የነፍሶቻቸዉን ንፍገት የሚጠበቁ ሰዎች ሁሉ እነዚያ እነርሱ ፍላጎታቸውን የሚያገኙ ናቸው።" - ቁርዓን 64፡16
ታማኝ መሆን፤
"እውነቱን ከውሸት ጋር አትቀላቅሉ። እናንተም የምታውቁ ስትሆኑ እውነትን አትደብቁ።" - ቁርዓን 2፡42
ትሁት መሆን፤
"(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለምዕመናን ንገራቸው አይኖቻቸውን ከማየት ይከልክሉ። ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ። ... ለምእመናትም ንገራቸው አይኖቻቸውን ያልተፈቀደን ከማየት ይከልክሉ። ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ። " - ቁርዓን 24፡30-31
አመስጋኝ መሆን፤
"አላህ ከእናቶቻችሁ ሆዶች ምንም የማታውቁ ሆናችሁ አወጣችሁ። ታመሰግኑ ዘንድም ለእናንተ መስሚያንና ማያዎችን ልቦችንም አደረገላችሁ
(ፈጠረለችሁ)። " - ቁርዓን 16፡78
ፍትሃዊ መሆን፤
"እናንተ በአላህ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! በትክክል (ለፍትህ) ቋሚዎች በነፍሶቻችሁ ወይም በወላጆችና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢሆንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ሁኑ። ሀብታም ወይም ድሃ ቢሆን..." - ቁርዓን 4፡135
ታጋሽ መሆን፤
"ታገስ አላህ የበጎ ሠሪዎችን ምንዳ አያጠፋምና።" - ቁርዓን 11፡115
መልካም መስራት፤
"እነዚያ በአላህ ያመኑና በጎ ስራዎችን የሰሩ ሰዎች ሁሉ አላህ ገነትን ቃል ገባላቸው። ለእነርሱ ምህረትና ታላቅ ምንዳ አለላቸው።" - ቁርዓን 5፡9
ማጠቃለያ
በጥቅሉ፥ ቁርዓን ብቸኛው እውነተኛ አምላክ እንዴት እንደሚመለክ የሰው ልጅን በማስተማር እውነተኛ የህይወት ዓላማውን እንዲያሳካ፥ ብሎም በዚህኛውም በወዲያኛውም አለም ስኬትን እንዲቀዳጅ ያስችለዋል።
"እኛ መጽሐፉን ባንተ ላይ ለሰዎች (ጥቅም) በእውነት አወረድነው። የተመራም ሰው ለነፍሱ ነው። የጠመመም ሰው የሚጠምመው (ጉዳቱ) በእርሷ ላይ ነው።" - ቁርዓን 39:41
ይህን የተከበረ መጽሐፍ ቢያንስ ማንበብ እንኳ የሚኖርብዎ አይመስሎትም?
