ነብይነት በእስልምና – النبوة في الإسلام

3.81 MB 161 1 Files
albyan
or download free
[free_download_btn]

Description

ኑህ፣ ኢብራሂም፣ ሙሳ፣ ኢሳ፣ ሙሐመድ

ሰላም በእነርሱ ላይ ይሁን

አላህ (አምላክ)፥ የአፅናፈ አለሙና በውስጡ ያለ ነገር ሁሉ ፈጣሪ፥ ሰዎችን ለአንድ ክቡር ዓላማ ፈጥሯል፤ እርሱን ብቻ እንዲገዙት እና በአስተምህሮቶቹ እና መመሪያው መሠረት ግሩም ሕይወት እንዲመሩ። ነገር ግን፥ ከአላህ ግልፅ መምሪያዎች ሳይደርሷቸው ሰዎች ይህን ዓላማ መሙላት አይችሉም።

አላህ፥ እጅግ አዛኙና እጅግ ፍትሃዊው፥ በአላማ ቢስነት ምድር ላይ እንድንባዝን አልተወንም። አላህ አላማችን እናውቁ ዘንድ፥ መልዕክቱን ለመላ የሰው ዘር የሚያስተላልፉና በተግባር የሚያሳዩ የሆኑ አይነት ግለሰቦችን ሾሟል። እነዚህም ግለሰቦች ነቢያት በመባል የሚታወቁ ሲሆን አደም፣ ኑህ፣ ኢብራሂም፣ ሙሳ፣ ኢሳ እና ሙሐመድ – ሰላም በሁሉም ላይ ይሁን – ይካተታሉ።

የነብያት ባህሪያት

ሁሉም ነብያት የተለዩ ምጡቅ የሰው ልጆች የሚያደርጓቸው የጋራ ባህሪያት አሏቸው።

ነብያት ራዕይ (መለኮታዊ መገለጥ) ይቀበላሉ

በተራ ሰው እና በነብይ መካከል ያለው ዋነኛው ልዩነት፥ ነብይ ከአላህ የሚወረድለትን ራዕይ መቀበሉ ነው።

ነብያት የላቀ ስብዕና አላቸው

ነብያት እንደሐብት፣ ከፍተኛ ደረጃ ወይም ሥልጣን የመሳሰሉ ግላዊ ጥቅሞችን ፈፅሞ አይፈልጉም፤ ይልቁንስ የአላህን ይሁንታ ብቻ ፈላጊዎች ናቸው።

ነብያት በስብዕናም ሆነ በፃድቅነት ከሕዝቦቻቸው መሃል ምርጦቹ ምሳሌዎች ናቸው። ከምጡቅ ስነ ምግባር ጋር አላህን በመታዘዝ ኖረዋል፤ እና በንግግርም ሆነ በጠባይ ሁልጊዜም እውነተኞች ነበሩ።

በዚህ ምክንያት፥ በአንዳንድ የሌሎች ሃይማኖቶች ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚታየውን አይነት ትላልቅ ኃጢአቶችን በሐሰት ለነብያት መስጠትን ሙስሊሞች ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርጋሉ።

ነብያት ተዓምራትን ይፈፅማሉ

ብዙ ነብያት ተዓምራትን ፈፅመዋል፤ ብዙውን ጊዜ ሕዝቦቻቸው ምጥቀትን ያሳዩ በነበረበት አንዳች የሙያ መስክ። ለምሳሌ፥ የሙሳ (ሰላም ይስፈንባቸው) ሕዝቦች በምትሃት (ማጅክ) ምጡቅ ነበሩ፤ ስለዚህ፥ ሙሳም (ሰላም ይስፈንባቸው) ምትሃተኞች እንኳ ማድረግ ያልቻሏቸውን ተዓምራዊ ድርጊቶች መፈፀም ይችሉ ነበር። የኢሳ (ሰላም ይስፈንባቸው) ሕዝቦች ደግሞ በፈውስ ጉዳዮች የተካኑ ነበሩ፤ ስለዚህ፥ ኢሳ (ሰላም ይስፈንባቸው) ከገዛ ሕዝባቸው ክህሎት የላቁ የማዳን ተግባራትን መፈፀም ችለው ነበር። የሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሕዝቦችም በስነ ግጥም ችሎታቸው የመጠቁ ነበሩ፤ ስለዚህ፥ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ማንም ገጣሚ ሊገዳደር ያልተቻለውን እጅግ የተቡ ቃላት የያዘውን ቁርዓን ይዘው መጡ። በተጨማሪም፥ በርካታ ነቢያት ወደፊት የሚከሰቱ እውነተኛ ትንቢቶችን አድርሰዋል። እንዲህ ያሉት ተዓምራት ሊፈፀሙ የቻሉት በአላህ ፈቃድና እገዛ ብቻ ነበር። ይህም ነቢያት መለኮታዊ ሳይሆኑ ሰዎች እንደነበሩ የሚረጋግጥ ነው።

ነቢያት መለኮታዊ አይደሉም

ነቢያት በኃያሉ አላህ የተመረጡ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፥ በምንም መንገድ ግን መለኮታዊ ስላልሆኑ መመለክ የለባቸውም። ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ እንዲህ እንዲሉ ታዘው ነበር፥

“እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ወደኔ የሚወረድልኝ ቢጤያችሁ ሰው ብቻ ነኝ።” (ቁርዓን 18:110)

ነቢያት መለኮታዊ እንዳልነበሩ እና አንድዬውን እውነተኛ አምላክ ይገዙና ይሰግዱለት እንደነበር በመፅሃፍ ቅዱስ፥ ብሉይም ሐዲስ ኪዳንም፥ እንኳ ተገልፆ ይገኛል።

"[ኢየሱስ] ጥቂትም ወደፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲፀልይ ..." (ማቴዎስ 26:39)

"እነርሱም [ሙሴና አሮን] በግምባራቸው ወድቀው..." (ዘኊልቊ 16:22)

"አብራምም [አብርሃም] በግምባሩ ወደቀ፥ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው ..." (ዘፍጥረት 17:3)

ነቢያት አስፈላጊ ባህሪያት አሏቸው

አላህ ሁሉንም ነቢያት ተልዕኳቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፅሙ እንደ ፅናት፣ ድፍረት፣ አመራር፣ ትዕግስት እና ጥበብ ያሉ የተወሰኑ ባህሪያትን ሰጥቷቸዋል።

የሚከተሉት አንዳንድ ምሳሌዎች ናቸው፦

• የኑህ (ሰላም ይስፈንባቸው) ሕዝቦቹን ወደ አላህ ሳይታክት የመጣራት ፅናት፥ ምንም እንኳ ጥቂቶች ብቻ ቢቀበሉም።

• የኢብራሂም (ሰላም ይስፈንባቸው) ገና ወጣት ሆነው ሳለ መላ ህብረተሰባቸውን ስለያዙት የተሳሳተ እምነት ብቻቸውን የተጋፈጡበት ድፍረት።

• የሙሳ (ሰላም ይስፈንባቸው) ከዘመናቸው እጅግ ጨቋኝ አምባገነን – ፈርዖን – ሕዝባቸውን በዘዴ ለማስመለጥ ያሳዩት አመራር።

• የኢሳ (ሰላም በሆነበት) በገዛ ሕዝባቸው የታወጀባቸውን የመከራና የሥቃይ ፍርድ የተቋቋሙበት ትዕግስት።

• የሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የቆየ የግጭት ታሪክ የነበራቸውን በርካታ የአረቢያ ተቀናቃኝ ጎሳዎችን አስማምተው ወደ አንድ ሰላማዊ ማህበረሰብነት የቀየሩበት ጥበብ።

የነቢያቱ መልእክት

"በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ ‘አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ’ በማለት መልዕክተኛን በእርግጥ ልከናል።" (ቁርዓን 16:36)

ሁሉም ነቢያት በአንድዬው እውነተኛ አምላክ የተላኩ በመሆናቸው፥ ሁሉም ተመሳሳይ መልዕክትን አድርሰዋል፤ ተልዕኳቸውም አንድ ነበር – ህዝቦቻቸውን ስለህይወት ዓላማ ማስታወስና ማስተማር።

መልእክታቸውም ይህ ነበር፦

• የአላህን እውነተኛ ፅንሰ ሃሳብ ግልፅ ማድረግና ሐሰተኛ እምነቶችን ማስተው

• የሕይወትን እውነተኛ ዓላማ ማስተማር

• አላህ እንዴት መመለክ እንደሚገባው በተግባር ማሳየት

• የአላህን የጽድቅና ኃጢዓተኛ ጠባዮች ብያኔ ማሳወቅ እና ህዝባቸውን በዚያ መሰረት መምከር

• የታዛዥነት ምንዳዎችን (ጀነት) መግለፅ እና የትዕዛዛት ጥሰት ቅጣትን (ጀሃነም) ማስጠንቀቅ

• ሰዎች በተለምዶ በተሳሳተ መንገድ የሚረዷቸው፥ እንደ ነፍስ፣ መላዕክት፣ አጋንንት፣ አኼራ እና እጣ ፋንታ የመሳሰሉ፥ ጉዳዮችን ማብራራት

"ከመልዕክተኛ ማንኛውንም ለእነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌላ አልላክንም። ..." (ቁርዓን 14:4)

የሁሉም ነቢያት ዋናኛ ትኩረት የአምላክን ፅንሰ ሃሳብ ግልፅ ማድረግ ነበር፤ አጋሮችም ሆኑ ብጤዎች የሌሉት መሆኑን፤ እናም ሁሉም አይነት አምልኮ ለእርሱ በብቸኝነት መደረግ እንደሚኖርበት። በቁርዓን ውስጥ፥ ይህንን መልዕክት የሚያወሱ በርካታ የነቢያት ምሳሌዎች ይገኛሉ፥

ኑህ (ሰላም ይስፈንባቸው) እንዲህ አሉ፦ (ቁርዓን 7:59)

“ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ። ለእናንተ ከርሱ ሌላ ምንም አምላክ የላችሁም።"

ኢብራሂም (ሰላም ይስፈንባቸው) እንዲህ አሉ፦ (ቁርዓን 21:66)

“’ታዲያ ለእናንተ ምንም የማይጠቅማችሁንና የማይጎዳችሁን ነገር ከአላህ ሌላ ትገዛላችሁን?’ አላቸው።”

ሙሳ (ሰላም ይስፈንባቸው) እንዲህ አሉ፦ (ቁርዓን 7:140)

“’ከአላህ ሌላ እርሱ ከዓለማት ያበለጣችሁ ሲሆን (የምትገዙት) አምላክን እፈልግላችኋለሁን?’ አለ።”

ኢሳ (ሰላም ይስፈንባቸው) እንዲህ አሉ፦ (ቁርዓን 3:51)

“’አላህ ጌታዬና ጌታችሁ ነው፤ ስለዚህ ተገዙት፤ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው’ (አላቸው)።”

ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፦ (ቁርዓን 18:110)

“’እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ወደኔ የሚወረድልኝ ቢጤያችሁ ሰው ብቻ ነኝ። የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤ መልካም ሥራን ይሥራ። በጌታውም መገዛት አንድንም አያጋራ’ በላቸው።”

ይህ መልእክት ከትውልድ ትውልድ ወጥ ነበር፤ እናም በአላህ ላይ ትክክለኛውን እምነት የመያዝን አስፈላጊነት ገልፆ ያሳያል።

ሁሉም ሕዝብ ነብይ ተልኮለት ነበር

"ለሕዝቦችም ሁሉ መልዕክተኛ አላቸው።" (ቁርዓን 10:47)

በሺዎች የሚቆጠሩ ነቢያት በየዘመኑ፥ ቢያንስ ለየህዝቡ አንድ አንድ፥ ለሰው ልጅ መመራት እንደእዝነት መላካቸውን ሙስሊሞች ያምናሉ።

በአንዳንድ ሁኔታዎች፥ የነቢያቱ መልእክት ጠፍቶ፣ ተበርዞ፣ ተረስቶ፣ ተትቶ፣ አልያም በሕዝቡ ተክዶ ነበር። እነዚህ የአላህን መልዕክት መልሶ የሚያደርስ አዲስ ነብይ እንዲላክ መንስዔ የነበሩ አንዳንድ ምክንያቶች ናቸው።

ሙስሊሞች በአላህ በተላኩት በሁሉም ነቢያት ያምናሉ፤ ያከብሯቸዋልም። ሙስሊሞች በተጨማሪም፥ ለነብያት በተወረዱት ሁሉም ቅዱሳን መፃህፍት ያምናሉ፤ ነገር ግን ከቁርዓን በስተቀር ከእነዚህ መፃህፍት አንዱም በወረደበት የመጀመሪያ ቅርፁ እንደማይገኝ ይገነዘባሉ።

"ከርሱ በፊት ያሉትን መጻሕፍት የሚያረጋግጥ ሲሆን መጽሐፉን (ቁርዓንን) ባንተ ላይ ከፋፍሎ በእውነት አወረደ። ተውራትንና ኢንጂልንም አውርዷል።" (ቁርዓን 3:3)

ሁሉም ሰው ለምን ራዕይ በቀጥታ አይወርድለትም?

ማን በፈቃደኝነት የእሱን መንገድ እንደሚከተልና ማን ደግሞ ወደ ጥመት እንደሚሄድ ለማየት መፈተኛ፥ አላህ ሕይወትን ፈጥሮ ለሰው ልጆች ነጻ ፈቃድን እና አስተውሎትን ሰጥቷል። እያንዳንዱ ሰው ራዕይ ቢወርድለት፥ ሕይወት እውነተኛ የእምነት መፈተኛ አትሆንም ነበር።

የአንድ ሰው እምነት እውነተኛው ፈተና የሚሆነው የአላህን ምልክቶች ለማስተንተንና ለመገንዘብ፥ ምንም ጉልበት ከማይጠይቀውና እምነትንም ትርጉም የለሽ ከሚያደርገው በአላህ በቀጥታ መነጋገር ይልቅ፥ የሰውየው አእምሮንና ምክንያትን መጠቀም ነው።

ነቢያት ምንም እንኳ ቀጥተኛ ራዕይ ቢቀበሉም፥ ይህ የሕይወት ፈተናዎች የማይነካቸው አላደረጋቸውም፤ ምክንያቱም ነብይነት አብሮ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችንና ፈተናዎችን ይዞ ስለሚመጣ።

የመጨረሻው ነብይ

ነቢያት ይላኩ የነብረው ለሆኑ የተለዩ የሕዝቦች ስብስብ ስለነበር፥ በጊዜ ብዛት፥ ይዘዋቸው መጥተው የነበሩት መልዕክቶች ወይ ጠፍተዋል ወይ ደግሞ ተበርዘዋል።

ነገር ግን ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ለሆኑ የተለዩ ሕዝቦች ብቻ አልነበረም የተላኩት፤ ለሰው ልጆች በመላ እንጂ። መልእክታቸውም በቁርዓንም በሱናዎቻቸውም መልክ በሚገባ ተጠብቆ ቆይቷል።

ቁርዓንና ሱናው በሚገባ ተጠብቀው ስላሉ እና ማንም ሰው በቀላሉ ስለሚያገኛቸው፥ የሌላ ነብይ መላክ አስፈላጊ አይደለም።

• ቁርዓን የአላህ የንግግር ቃል ሲሆን፥ ከማንኛውም አይነት ብረዛ፣ ስህተቶች ወይም መጣረሶች ነፃ ነው። “ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) የሚለይ ..." (ቁርዓን 2:185) መፅሃፍም ነው።

• ሱና የነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ንግግሮችና ድርጊቶች ስብስብ ሲሆን፥ በባልደረቦቻቸው እና በእነርሱ ተማሪዎች በሚገባ ተዘግቦ ተቀምጧ። በሽህዎች የሚቆጠሩ የእነዚህ ሐዲሶች የመዘገብ እና በስርዓት ተመርምረው የመረጋገጥ እውነታ ለማንም ሰው ነብዩ ሙሐመድን (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በትክክል ለመከተል በጣም ቀላል ያደርገዋል።

የነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መልእክት ከቀደሙት ነቢያት አስተምህሮቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የተጣጣመ ሲሆን መልእክታቸውንም መልሶ ያረጋግጣል።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)፥ ከዘመናቸው ጀምሮ እስከ አለም ፍፃሜ ድረስ አሁን ያለውን እና ወደፊት የሚመጡትን ትውልዶች ጨምሮ፥ ለሰው ለመላው የሰው ዘር የተላኩ የመጨረሻው ነብይ ናቸው። ታማኝ፣ ፍትሐዊ፣ አዛኝ፣ ሩህሩህ፣ እውነተኛ እና ጀግና የሰው ልጅ ፍፁም ምሳሌ ነበሩ። ከእርሳቸው በፊት እንዳለፉት ሌሎች ነቢያት ሁሉ፥ አንድም አይነት ክፉ ጠባይ አልነበራቸውም፤ ተጋድሏቸውም ለአላህ ብቻ ነበር።

ማጠቃለያ

"ለእናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለሆነ ሰው፣ አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል አልላችሁ።" (ቁርዓን 33:21)

ነቢያት እንደ እዝነት ሆነው ነበር በአላህ የተላኩት፤ የእርሱን መልዕክት እንዲያደርሱ እና እንዴት የፃድቅ ህይወት እንደሚኖሩ ሰዎችን እንዲያስተምሩ። እጅግ ምርጥ ባህሪያት ያሏቸው ሲሆኑ፥ እነርሱን መከተል እና መታዘዝ የተገባ ነው።

ነብይን መከተል ለአላህ መታዘዝ ሲሆን፥ ነብይን አለመቀበል ደግሞ አላህ አለመታዘዝ ነው። ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከነብያት የመጨረሻው ናቸው፤ በእርሳቸው መምጣትም የአላህ መመሪያ ምሉዕ ሆኗል፤ እናም መዳናችን ለአላህ እና ለመጨረሻ ነቢዩ በመታዘዝ ተፈፃሚ ነው።

Similar Downloads

No related download found!