Description
አላህን መገዛት፣ ጨዋነት፣ ክብር
ሂጃብ ምንድነው?
ሂጃብ የሚለው ቃል የተመሰረተው መደበቅ ወይም መሸፈን የሚል ፍችን ከሚሰጠው ‘ሐጀበ’ የሚል የአረቢኛ ስርወ ግስ ነው።
በኢስላማዊ መቼት ውስጥ፥ ሂጃብ ለአካለ መጥን የደረሱ ሙስሊም ሴቶች እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸውን የአለባበስ ደንብ ያመለክታል።
ሂጃብ ከፊትና እጆች በስተቀር መላ ሰውነትን የመሸፈን ወይም የመጋረድ አግባብ ነው።
አንዳንዶች በተጨማሪ ፊታቸውንም እና እጆቻቸውንም መሸፈን ይመርጣሉ፤ ይህም አለባበስ ቡርቃ ወይም ኒቃብ በመባል ይጠራል።
ሴቶች እና የተወሰኑ ወንድ ዘመድ አዝማድ ብቻ በሚገኙባቸው ሁኔታዎች ሂጃብ መልበስ ግዴታ አይደለም።
ነገር ግን፥ ሂጃብ ስለውጫዊ ገፅታዎች ብቻ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም፤ ስለ መልካም ንግግር፣ ስለ ጨዋነት እና በአክብሮት ስለተሞላ ጠባይም ጭምር እንጂ።
እነዚህ ደጋግ ጠባዮች ከወንዶችም የሚጠበቁ ናቸው።
ሙስሊም ወንዶችም እየተከበሩና ውስብስብ እንዲሆን ልብስ መልበስ አለባቸው።
ሂጃብ ታዛዥነት ነው።
ምንም እንኳ ሂጃብ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ቢሆንም፥ ከምንም ነገር በፊት በቅድሚያ ከአላህ የመጣ ትእዛዝ ው። ስለዚህ፥ እሱን መልበስ የእምነት እና አላህን የመታዘዝ ተግባር ነው፤ በቁርዓን ውስጥ እንደተገለፀው፥
"አንተ ነቢዩ ሆይ! ለሚስቶቸህ፣ ለሴቶች ልጆችህም፣ ለምእመናን ሚስቶችም ከመከናነቢያዎቻቸው በላያቸው ላይ እንዲለቁ ንገራቸው።" ቁርዓን 33፡59
አላህ፥ እጅግ ብልሁ፥ ለፍጥረቱ የሚበጀውን ነገር አዋቂ ሲሆን የሰው ዘርን ለመጥቀም መመሪያን አቅርቧል። እንደሌላ ማንኛውም ለፈጣሪ የመታዘዝ ተግባር ሁሉ፥ሂጃብ መልበስም ግለሰቡን ወደጌታው ለማቅረብ ይረዳል ብሎም በላባሹ ላይ የእርካታ ስሜትንና መብቃቃትን ለማምጣት ያግዛል።
ሂጃብ በምንም መንገድ ሴቶች ከወንዶች ያነሱ መሆናቸውን አይጠቁምም።
ሂጃብ ጨዋነት ነው።
እስልምና ጨዋነትንና ንፅህናን የሚያራምድ ሲሆን በማህበረሰብ ውስጥ የስነምግባር ልቅነትን ለመቀነስ ይፈልጋል። ሂጃብም፥ ሌሎች ነገሮች ጨምሮ፥ ይህን ግብ ለማሳካት ያግዛል።
"ለምእመናን ንገራቸው፡- ዓይኖቻቸውን (ያልተፈቀደን ከማየት) ይከልክሉ፤ ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ፤ ይህ ለነሱ የተሻለ ነው፤ አላህ በሚሠሩት ሁሉ ውስጥ ዐዋቂ ነው። ለምእምናትም ንገራቸው፡- ዓይኖቻቸውን ይከልክሉ። ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ። ጌጣቸውንም ከእርሷ ግልጽ ከሆነው በስተቀር አይግለጡ። ጉፍታዎቻቸውንም በአንገትጌዎቻቸው ላይ ያጣፉ። ..." ቁርዓን 24፡30-31
ከላይ በተጠቀሱት አንቀፆች፥ እይታቸውን በመስበርና ጨዋነታቸውን በመጠበቅ ረገድ ቀድመው የተጠሩት ወንዶች መሆናቸውን አስታውሱ። ይህም እንዲህ አይነቱን ጨዋነት የማስጠበቅን ሙሉ ሐላፊነት ሴቶች ናቸው የሚሸከሙት የሚለውን የተለመደ ወቀሳ ያስተባብላል።
እስልምና ጨዋነት የጎደለው አለባበስ እና ተራክቧዊ ባህሪ ባደባባይ ማሳየትን ሲያወግዝ፤ ተግባራዊ ሐይማኖት እንደመሆኑ መጠን እስልምና በባለትዳር ጥንዶች መካከል ግላዊነቱን የጠበቀ ፍቅር፣ ውዴታና ተራክቦን ያበረታታል።
ሂጃብ መከላከያ ነው
ከሂጃብ ጀርባ ያለው ጥበብ፥ በማህበረሰብ ውስጥ የሚከሰትን ተራክቧዊ ልቅነት እና የሞራል ዝቅጠት ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች በተቻለ መጠን መቀነስ ነው። ሂጃብ በቤተሰቦችም በህብረተሰቦችም ውስጥ በተለያዩ መንገዶች መረጋጋትን በመፍጠር ወንዶች፣ ሴቶች እና ማህበረሰብ እንዲጠበቁ ያግዛል፦
ከማይፈለጉ ጉንተላዎች ይከልላል።
ሴቶችን ካፈንጋጭ እይታዎች እና ውጫዊ ብርበራ ይከልላል።
በሴቶች ላይ የፆታ ጥቃት የመሰንዘር እድልን ለመቀነስ ሊያግዝ ይችላል።
ሴቶችን በአካላዊ ቅርፅ ላይ ከተመሰረተ ፆታዊ ብዝበዛ ይከልላል።
ከስጋዊ ውስዋሶች እና ጎጂ ፍላጎቶች ይከልላል።
ሂጃብ ክብር ነው።
ሂጃብ የሴትን ሴታዊነት ከማፈን ይልቅ ያጎላል፤ ብሎም ሴቶችን፥ እንደ አካላዊ ቅርፅ በመሰሉ የላይ ላይ መለኪያዎች ከመገመት በተቃራኒው፥ በማንነታቸው መኩራትን እና ራስ ማክበርን ያላብሳል።
ይህም ሴቶችን፥ እንደሰውነት ቅርፅና የገቢ መጠን በመሳሰሉ ቁሳዊ መንገዶች አማካይነት ዋጋቸውን በሸማች ማህበረሰብ ከማስገመት ይልቅ፥ ፈሪሃ አምላክ፣ እውቀት እና ማህበረሰባዊ አስተዋፅዖን በመሳሰሉ ይበልጥ ትርጉም በሚሰጡ ደረጃዎች በኩል የራሳቸውን ክብር የመቅረፅ ኃይል ያቀዳጃል።
በአላህ ፊት፥ ሴቶችና ወንዶች እኩል ለመሆን አንድ አይነት መሆን አይጠበቅባቸውም፤ ይህም ለያንዳንዳቸው ተግባራዊነት ባላቸው የተለያዩ ሚናዎች እና ሐላፊነቶች ተንፀባርቋል።
የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ፥ ተወኩል ካርመን፥ "የየመን አቢዮት እናት"፥ ስለሂጃቧ እና ካላት የእውቀትና የትምህርት ደረጃ ጋር ምን ያህል እንደማይመጥን በጋዜጠኞች በተጠየቀች ጊዜ እንዲህ ስትል መልሳለች፤
"የሰው ልጅ በድሮ ጊዜያት እርቃኑን ነበር፤ እናም አእምሮው እያደገ ሲመጣ ልብስ መልበስ ጀመረ። ዛሬ እኔ የሆንኩት እና የለበስኩት አለባበስ የሰው ልጅ የደረሰበትን እጅግ የላቀ የአስተሳሰብና የስልጣኔ ደረጃ ይወክላል፤ እና ደግሞም ወደ ኋላ መንሸራረት አይደለም። አሁንም ቢሆን አልባሳትን አስወግዶ መራቆት ነው ወደ ጥንታዊ ጊዜያት የኋሊት መንሸራተት የሚሆነው።"
ሂጃብ ክብር ነው።
በብዙ ማህበረሰቦች ውስጥ በዛሬው ጊዜ፥ በርካታ ሴቶች ያላቸው የተፈላጊነት ዋጋ ካላቸው መስህብ ጋር እንደሚዛመድ ከለጋነት እድሜያቸው ጀምሮ እንዲማሩ በመደረግ ላይ ናቸው። ኢምክንያታዊ የሆኑ የእኩዮች ግፊትን እና የህብረተሰብ ጥበቃዎችን ለማሟላት ብለው የማይጨበጡና አዋራጅ የውበት መለኪያ ደረጃዎችን ለመከተል ይገደዳሉ።
ይህን በመሰለ ለውጫዊ ውበት ከፍተኛ አፅንዖት በሚሰጥ የላይ የላይ (ግልብ) ከባቢ፥ የግለሰቡ ውስጣዊ ውበት ከቁጥር የሚገባው በጣም በጥቂቱ ነው።
እስልምና ግን፥ ሴት ልጅ፥ ጥቂትን እንጂ ልትቀትይረው በማትችለው፥ መልኳ ወይም አካላዊ መስህቦቿ ሳይሆን በጨዋ ጠባይዋና ምግባሮቿ መሰረት እንደምትከበር እስልምና ያስተምራል።
በማህበረሰብ ዘንድ እውቅናን ወይም ተቀባይነት ለማግኘት አካሏን እና ሴትነቷን መጠቀም አይጠበቅባትም፤ ሂጃብ ግለሰባዊ ዋጋን ከአካላዊ መስህብ በማራቅ እንደ አማኝነት፣ መልካም ጠባይ፣ ጨዋነት እና አእምሯዊ ብቃት፥ ሁሉም ሰው ይበልጥ በእኩል ደረጃ ሊታደላቸው የሚችሉ ባህሪያት፥ የመሳሰሉ ምርጥነቶች ላይ እንዲያመራ ያደርጋል።
ሂጃብ በመጽሐፍ ቅዱስ!
ሂጃብ አዲስ ነገር አይደለም። ሙስሊም ሴቶች እንደኢየሱስ እናት ማርያም አይነቶችን የቀድሞ ዘመን ብፁዓን ሴቶች ምሳሌ ይከተላሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ማስረጃዎች ውስጥ የሚከተሉት ሁለት አንቀፆች ይካተታሉ:
"ራሷን ሳትሸፍን ኝ የምትፀልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራሷን ታዋርዳለች።" 1 ቆሮንቶስ 11:3-6።
"እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።" 1 ጢሞቴዎስ 2:9-10.
ሂጃብ በራስ መተማመን ነው።
ሂጃብ ሴቶችን ሰው እንደመሆናቸው በራሳቸው እንዲተማመኑ ያስችላቸዋል። በሕይወት ውስጥ አንገብጋቢዎቹ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ በመፍቀድ የሴቶችን የራስ አክብሮት ያሳድጋል። ተክለ ቁመና ላይ የበዛ ጥማተኛነት አደገኛ እና ጤናማ ያልሆኑ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል፤ ከጊዜ ወደጊዜ ፍላጎቱ እየተለጠጠ ባለ ማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነትን ለማረጋገጥ አንዳንድ ሴቶች ምን ያህል ጎጂ ርቀቶችን እስከመሄድ መድረሳቸው ሲታይ። ውጫዊ ገፅታ ላይ የተመሰረተን ግለ ንቃተ ህሊና በመገደብ ከራስ መተማመን ማጣት ጋር የሚያያዙ እንዲህ ያሉ አእምሯዊና አካላዊ ጉዳቶች ለመከላከል ሂጃብ ያግዛል።
"ስለተጨቆንኩ አይደለም የምለብሰው፤ የምለብሰው ስለሚያጎለብተኝ ነው።" - ጁማና፣ 23፣ ሜልቦርን።
ሂጃብ ... አይደለም
· ለማኅበረሰብ አስተዋፅዖ ማድረግን አያግድም።
· የጭቆና ምልክት አይደለም።
· ሴቶች እና ወንድ የቅርብ ዘመድ አዝማድ ብቻ ባሉባቸው ስፍራዎች መለበሱ ግድ አይደለም።
· ሴት ከወንድ እንደምታንስ የሚያሳይ ምልክት አይደለም።
· የሴትን ልጅ ምልከታዎቿንና ሐሳቦቿን የመግለፅ ነፃነት መገደቢያ ዘዴ አይደለም።
· ሴቶችን ትምህርታቸውን አልያም የሚስማማቸውን ሙያ እንዳይከታተሉ የመገደቢያ ዘዴ አይደለም።
· ተንቀሳቃሽ ወህኒ ቤት አይደለም።
· ሙስሊም ያልሆኑን ማግለያ፣ መጋጫ አልያም መቃወሚያ አይደለም።
· አዲስ ነገር አይደለም፤ በታሪክ ውስጥ በብዙ ቅዱሳን ሴቶች ሲተገበር የኖረ ነው።
· ከህብረተሰብ እሴቶች ጋር ተፃራሪ አይደለም - ሰዎች በአለባበሳቸው ጀጅ መደረግ እንደሌለባቸው ብሎም በልብስ ምርጫቸው አልያም በመልካቸው እንዳይገለሉና ያላግባብ እንዳይስተናገዱ የህብረተሰብ እሴቶች ያስገድዳሉ።
· ሰዎችን ማብራራት እና ከማኅበረሰብ መለየት አይሆንም።
ሙስሊም ሴቶች ስለሂጃብ ምን እንደሚሉ
"እኔ በ17 አመቴ ነበር መጀመሪያ የለበስኩት፥ እና አሁን ላይ ቀደም ብዬ አለመልበሴ ይቆጨኛል።" ፋተን፣ 27፣ ሜልቦርን።
"ቁም ነገሩ ለመልበስ በቂ ዝግጂት አለማድረጋችን አይደለም፤ ጉዳዩ ለመልበስ በበቂ ሁኔታ እድለኛ ስለመሆናችን ነው።" መዲና፣ 22፣ ሜልቦርን።
"ሂጃብ መልበስ ነጻነቴን እና ምርጫዬን እንጂ፥ ወንዶች እና ብዙሃን መገናኛ እንደሚፈልጉት መታፈኔን አይደለም የሚወክለው።" ኑሰይባህ፣ 45፣ ሜልቦርን።
"ሂጃብ መልበስን እወዳለሁ፤ ምክንያቱም ለአላህ ብዬ ስለማደርገው እናም ሁሌ ያንን ባሰብኩ ቁጥር ፊቴ በፈገግታ ይሞላል።” አዒሻ፣ 13፣ ሜልቦርን።
"ስለወንዶች በርባሪ አይኖች ሳልጨነቅ አላማዬን ለማሳካት ወደሙያ ስምሪቴና ወደ ት/ቤት እንደፈለግኩ እንድንቀሳቀስ ያስችለኛል። በአስተሳሰቤ እና በባህሪዬ እንጂ በአለባበሴ ላይ ተመስርተው ሰዎች እንዳይገምቱኝ ያስገድዳቸዋል።” ወ/ሪት ፍላቪያ፣ 22፣ ዩ ኤስ ኤ
“ሰውነቴ የግል ጉዳዬ ነው፤ አለባበሴን ለማንም ማስረዳት አይኖርብኝም ነበር። የሐይማኖቴ አንድ አካል ነው። ያንን ለመልበስ መምረጤ ከሌላው ያነስኩ ሴት አያደርገኝም።” ወ/ሪት ያስሚን፣ 21፣ አውስትራሊያ
ማጠቃለያ
ሂጃብ መልበስ ሙስሊሟ ሴት እና በፈጣሪዋ መካከል የታዛዥነት ተግባር ነው።
የኃይልና የክብር ምንጭ ነው፤ እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊም ሴቶች ሂጃብ መልበስን የእምነታቸው አንድ አካል አድርገው ይምርጡታል።
ከመጨቆን በራቀ መልኩ፥ ሂጃብ የነጻነት፣ የንፁህነት፣ እንዲሁም ከምንም በላይ ደግሞ የእምነት መግለጫ ተግባር ነው።
ሴቶችን ማክበር በእስላም ትምህርቶች ውስጥ አስፈላጊ ክፍል ነው፣ እና ይህ በሂጃብ ይታያል።
ሴቶች ተቀባይነት ለማግኘት ራሳቸውን መራቆት ሳይኖርባቸው እንዲሁም የገዛ አካላቸውን ለራሳቸው የማድረግ ውሳኔያቸውንም ለምን መባል ሲያቆሙ ነው እውነተኛ እኩልነት የሚከሰተው።
